አቶ በቀለ ገርባ ብልጽግና ፓርቲ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እንደከፈተባቸው ተናገሩ።

በሕወሃት የአስተዳድር ጊዜ በእስር ቤት የደረሰባቸው አካላዊ ጥቃት አለመኖሩን ፣በዚህ ንግግራቸው እንደማይጸጸቱ እና ይቅርታ እንደማይጠይቁም አቶ በቀለ ነግረውናል።

የብልጽግና ፖርቲ በፌስቡክ ተከፋዮቹ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶብኛል ሲሉም ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረንስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ በቀለ እንዳሉት “ አዎ በእስር ቤት በነበረኩበት ጊዜ ሳልመታ ነው የወጣሁት ይህንን ደግሜ እላለሁ ለዚህ ደግሞ ይቅርታ አልጠይቅም ” ብለዋል፡፡

“ይህ የሆነው ግን እድለኛ ስለነበርኩ እንጂ በጣም ብዙ ሰዎች አካላቸውን እና ህይወታቸውን እንዳጡ የቅርብ ምስክር ነኝ” ብለዋል፡፡

በተደጋጋሚ እኔ የምናገረውን ነገር አውዱን በማሳጣት ተገቢ ያልሆነ ወቀሳ እንዲነሳብኝ በቀድሞ ኦፒዲዮ በአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ ዘመቻ ተከፍቶብኛል ሲሉም ይናገራሉ፡፡

“አብረውኝ ታስረው የነበሩ እና በእስር ቤቶች እስርና ድብደባ እንዳይፈጸም የታገልን ሰዎች አሁን የብልጽግና ዋነኛ ደጋፊ የፌስቡክ አምደኞች የእኔን ሀሳብ የተለየ ቀለም እንዲኖረው በማድረግ ስሜን እያጠፉት ነው” የሚሉት አቶ በቀለ በቀደመው ዘመን የህወሃትን አምባገነንነት ዘመን ከታገሉት እና ከተንገላቱት ሰዎች አንዱ ነኝ ሲሉም አብራርተዋል።

“ከለውጡ በፊት ወደ ፍርድ ቤት ስንሄድ ጥቁር ለብሰን ነበር ኃላ ላይ ግን ልብሱን አውልቀን ሌላ ልብስ እንድንለብስ ብንጠየቅም እንቢ በማለታቸው እየተጎተትን መኪና ውስጥ እንድንገባ ተደርገናል እንጂ አልተመታንም” ሲሉ መልሰውልናል፡፡

“መጠየቅ ካለበት እንደውም ከህውሀት በላይ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እንደ ኦዲፒ ያለ ሀጢያተኛ የለም እንነጋገር ከተባለ የሚወጣ ብዙ ሚስጢር አለ፣ሆን ብለው ነው የሚነካኩን በእኛ ደም እነርሱ መጽደቅ አመላቸው ነው” ሲሉ የቀድሞው ኦዲፒ ወይም ብልጽግና ፓርቲን ተችተዋል አቶ በቀለ፡፡

መቀሌ በተደጋጋሚ ለምን ጉዳይ ነው የሚሄዱት? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም “እኔ የሄድኩት አንድ ጊዜ ብቻ ነው እሱንም ለአካዳሚ ጉዳይ ፣ከዛውጪ ድርሽ ብዬ አላውቅም” ሲሉም አቶ በቀለ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በያይኔአበባ ሻምበል
ግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.