የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና መምህር ናቸው ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሲታወሱ

የመጀመርያው የኢትዮጵያ የቀዶ ጥገና ሀኪም ናቸው፣በሀገራችን ከፍተኛ የህክምና ግልጋሎት የሚሰጥበትን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን አቋቁመዋል፣ ፈረንጆች ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እርሳቸው ጋር ይታከሙ እንደነበር ይገለፃል፣ በሀገሬው ሰውማ በታዋቂ ቀዶ ጥገና ሀኪምነታቸው ምክንያት እስከ መመለክም ደርሰው ነበር ይላሉ አንዳንድ ፀሀፍያን፣ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ፣ የእንግሊዝ እና የዓለም ሀኪሞች ማህበር አባል እና መሪም ነበሩ፣ በቀዶ ጥገናው ዘርፍ ላበረከቱት በጐ አስተዋፅኦ አምስት ኒሻኖችን ተሸልመዋል፣ በ1983 ዓ.ም ከራሳቸው አንደበት እንደተደመጠው ቀዶ ጠጋኝ ሀኪምና መምህር ብቻ ሳይሆኑ አውሮፕላን አብራሪም ነበሩ፣ በዲያቆንነታቸውም ቤተክርስትያን አገልግለዋል፣ እረ ስፖርቱንም ችላ አላሉት ግብፅ ለትምህርት በነበሩበት ወቅት የራግቢ ተጨዋችም ነበሩ፡፡

የዚህና የሌሎች በርካታ አንቱ የሚያስብሉ መልካም ስራዎች ባለቤት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን አንቱ ብለን በክብር ታሪካቸውንና አስተዋፅኦዋቸውን እናነሳለን፡፡

ከ1933 ዓ.ም በኋላ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቀዶ ጥገና ሀኪም የሆኑት ፕሮፊሰር አስራት ወልደየስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታየ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍ ይዋሉ ፅጌ ሰኔ12 ቀን 192ዐ ዓ.ም ነበር በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡

ትውልዳቸው አዲስ አበባ ቢሆንም ያደጉት ድሬድዋ ነው፡፡ በድሬድዋ የህፃንነት ቆይታቸው የአብነት ትምህርት በመማር ዳዊት ደግመዋል፡፡ የድሬድዋ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ዲያቆን በመሆንም አገልግለዋል፡፡

የካቲት 12 ቀን 1929 ማርሻል ግራዝያኒ ብዙ ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በግፍ ሲጨፈጭፍና፤ሲያስር ሰላባ ሆነው ህይወታቸውን ካጡት መካከል የያኔው የ 8 ህፃን ፕሮፌሰር አስራት አባት አቶ ወልደየስ አልታየ ይገኙበታል፣ አያታቸው ቀኝ አዝማች ፅጌ ወረደም ወደ ጣሊያን ሀገር በግዞት ተወስደው ታስረዋል፡፡

እናታቸው ወይዘሮ በሰልፍ ይዋሉ ፅጌም በምድር ላይ ብዙም አልቆዩም ነበርና የፕሮፌሰር አሥራት የልጅነት ጊዜ በሀሴት የተሞላ አልነበረም፡፡

በድሬድዋ ከአጐታቸው ጋር ከቆዩ በኋላ በ1934 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ በ1934 ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ቀጥለው በ1935 ዓ.ም የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ፕሮፌሰር አሥራት በትምህርታቸው ያስመዘግቡ የነበረው የላቀ ውጤት ወደ ግብፅ ሄደው በቪክቶሪያ ኮሌጅ እንዲማሩ አስቻላቸው፡፡ ከዚያም ወደ እንግሊዝ በማቅናት የህክምና ትምህርታቸውን ኤዴንበርግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል፡፡ በእንግሊዙ ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ሰርጀን ቀዶ ጥገናን ለይተው /ሰፔሻላይዝ አድርገው/ በሙያው ተክነው ነበር ወደ ሀገራቸው የተመለሱት፡፡

በ1947 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በልዕልት ፅሀይ ሆስፒታል /በአሁኑ ጦር ሀይሎች/ መስራት ጀመሩ፡፡ ፈረንጆች ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በፕሮፌሰር አስራት ይታከሙ እንደነበር ይገለፃል፡፡ በታዋቂ ቀዶ ጥገና ሀኪምነታቸው በሀገሬው ሰው እስከ መመለክም ደርሰው ነበር፡፡

የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና መምህርም ሆኑ፡፡ ከመምህርነታቸው ባሻገር በሀገራችን ከፍተኛ የህክምና ግልጋሎት የሚሰጥበትን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን አቋቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ፣ የእንግሊዝ እና የዓለም ሀኪሞች ማህበር አባል እና መሪ የነበሩት ፕሮፌሰር አስራት፤ በቀዶ ጥገናው ዘርፍ ላበረከቱት በጐ አስተዋፅኦ አምስት ኒሻኖችን ተሸልመዋል፡፡

በ1950ዎቹ የጤና ሚኒስትር ሆነው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ቢጠየቁም የነፍስ ጥሪዬ የህክምና ሙያ ነው በማለት ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡

በደርግ ጊዜ ፕሮፌሰር አስራት የሶሻሊዝም ሰባኪ እንዲሆኑ ተፈልጐ እንደበርና እሳቸው ግን ፍላጎቱን ባለማሳየታቸው ከደርግ ጋር የተፈጠረው ቅሬታ ንጉሰ ነገስት ሀ/ስላሴ እንዴት እንደሞቱ ላላወቀው ህዝብ “በልብ በሽታ እንደሞቱ ተናገር” ፕሮፌሰር አስራት ሲባሉ አሻፈረኝ በማለታቸው ከደርጎች ጋር የለየለት ቅዋሜ ውስጥ ገቡ፡፡

የህይወት ታሪካቸውን አንፀባራቂው ኮከብ በሚል ርዕሰ የከተበው አቶ ጋሻው መርሻ እንደሚለው ፕሮፌሰሩ “ለደርግ ትዕዛዝ አሻፈረኝ በማለታቸው ወደ ሰሜን ግንባር ምፅዋ ተልከው እንዲገደሉ ተፈልጐ ነበር፡፡

ወታደሩን ለማከም ወደ ምፅዋ የሄዱት ፕሮፌሰር አስራት ለልብ ድካም ቢዳረጉም በጥይት ሳይመቱ ተመልሰዋል፡፡ “በህክምና ሳይንስ ጠላት የለም፡፡ ጃንሆይንም፤ የደርግ ባለስልጣናትንም ያለምንም ልዩነት አክማለሁ፡፡ ህክምና የሰውነት ስራ ነው” ይላሉ፡፡

ጃንሆይን ማከማቸው በደርግ እንደተጠላው ሁሉ፤ የደርግ ባለስልጣናትን ማከማቸው ደግሞ በነ ህዋኃት እና መሠል ድርጅቶች አልተወደደላቸውም፡፡ ደርግ ፊውዳላዊ አድርጐ ሲያሳድዳቸው፣ ኢህአዴግ ደግሞ ደርግ አድርጐ ቆጥሯቸዋል፡፡

ግንቦት 2ዐ ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባን ኢህአዴግ ሲቆጣጠር በሽግግር መንግስቱ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ከእነ አቶ መለስ ዜናዊ እና ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም የብሄር ፌዴራሊዝም አስቸጋሪነቱን የኤርትራ መገንጠልም ለዘላቂ ሰላም እንደማይበጅ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ “ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚቅበዘበዙ ሁሉ እነሱ ቀድመው ይጠፋሉ፡፡” በሚለው ዝነኛ ንግግራቸውም ይታወቁ ነበር፡፡

አማራውን በጨቋኝነት ፈርጆ፣ ኢትዮጵያዊነትንም ጠልቶ የተጠነሰሰው የዘውግ ፖለቲካ ፕሮፌሰር ፈስራት ነሳኝ አሉ፡፡

አማራ ባለመደራጀቱ እረኛ እንደሌለው ከብት ተበትኖ የሀገር ውስጥ ስደተኛ ሆነ፣ ተፈናቀለ በማለት የህክምና ጋውናቸውን አውልቀው፣ ይጠሉት ወደነበረ የብሄር ፖለቲካ ገቡ፡፡
ጥር 1984 የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትን መሰረቱ፡፡ ፖለቲካውን ከተቀላቀሉ በኋላ በፕሮፊሰር አስራት ላይ ተደጋጋሚ ወከባ ይደርስባቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ በ1985 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩት 42 መምህራን መካከል ፕሮፌሰሩ ቀዳሚው ነበሩ፡፡

በዚህ ብቻ አላባራም በደብረ ብርሃን ከተማ ቀስቃሽ ንግግር በማድረግ እና ከጐጃም ገበሬዎች ጋር ለመፈንቅለ መንግስት አሲረዋል በሚል አምስት ዓመት ከ ስድስት ወር ተፈረደባቸው፡፡ በማረሚያ ቤት እያሉ ግፍና መከራን ተቀበሉ፡፡ ህክምናም ተከልክለዋል፡፡

የመሰረቱት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲያገለግላቸው እንዳልተፈቀደ አንፀባራቂው ኮከብ በሚለው መፅሀፉ የሚናገረው አቶ ጋሻው መርሻ ፕሮፌሰር አስራት 150 ጊዜ ፍርድቤት እንደቀረቡ ፅፏል፡፡ በመጨረሻ ከደከሙ በኋላ በመአህድ እና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጥረት በ1991 ዓ.ም ለህክምና ወደ አሜሪካ ቢሄዱም ሊተርፉ አልቻሉም፡፡

አሜሪካ አርፈው አዲስ አበባ ባለወልድ ቤተክርሲቲያን ስርአተ ቀብራቸው በ1991 ዓም ተፈፅሟል፡፡

በመአህድ አማካኝነትም ለበጐ አድራጐት የሚተጋ የፕሮፌሰር አስራት ፋውንዴሽን ተቋቁሟል፡፡

“ፕሮፌሰር አስራት በህክምና፣ ሀገርን በመውደድ እና ራስን አሳልፎ ለህዝብ በመስጠት አርአያ ሰው ናቸውና ፋውንዴሽኑ ተገቢ ነው” ይላል የህይወት ታሪክ ከታቢያቸው አቶ ጋሻው መርሻ፡፡

ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን በቅርብ የሚያውቋቸው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ
ፕሮፌሰር አስራት ኢትዮጵያን በተለየ መንገድ ይወዷታል፡፡ ስለሚወዷት ጎሰኝነትን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ደፋር ነበሩ፡፡

የሚገርምህ ጃንሆይን በእስር እንዳሉ መርምረዋቸው ነበር፡፡ጤነኛ ሆነው አገኟቸው፡፡ወዲያው ግን ደርግ ገሎ ታመው እንደሞቱ መስክር አላቸው፡፡ደህና ነበሩ፡፡ ውሸት አልናገርም ብለው ደርግን ሞግተው ጃንሆይን ደርግ እንደገደላቸው ታወቀ፡፡

ያን ባያደርጉ ይሄኔ የደርግ ገዳይነት ተሸፍኖ ህዝቡ ጃንሆይ ታመው ሞቱ የሚለውን ያምን ነበር ሲሉ መስክረውላቸዋል፡፡

ስለ አበርክቶዎትና ስለመስዋዕትነትዎት ፕሮፌሰር አሥራት አንቱ ስንል እናከብርዎታለን!!!

በሔኖክ አስራት

2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *