የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ሕወሃት ምርጫውን አካሂዳለሁ ባለው ጊዜ ቢያካሂድ ምን ሊፈጠር ይችላል?

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ እና መንግስታቸው የዘንድሮውን አገር አቀፍ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ማካሄድ እንደማይችል ማሳወቁ ይታወሳል።

የትግራይ ክልልን እየመራ ያለው ህወሀት ግን ኮሮና ቫይረስን እየተከላከልን ክልላዊ ምርጫውን አካሂዳለሁ የሚለውን አቋሙን እንደማይቀይረው በድጋሚ አሳውቋል።

ህወሓት ምርጫን በሚመለከት የወሰደው አቋም ፖለቲካዊና ህገመንግሰታዊ ነው፣ ፌዴራል መንግስት ምርጫ ሊያካሂድ እንደማይችል በማስታወቁ በክልል ደረጃ ግን የኮሮናን ወረርሽን እየተከላከልን በጥንቃቄ ምርጫውን ማካሄድ እንችላለን ሲል በአቋሙ እንደሚገፋበት ዶ/ር ደብረፂዮን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም ትግራይ ክልልን እየመራ ያለው ፓርቲ በዚሁ አቋሙ ከገፋበትና ወደ ተግባር ከገባ የፌደራል መንግስት ህጋዊ እርምጃ ምን ሊሆን ይችላል ሲል የህግ ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡

ባለሙያዎቹ ፌደራል መንግስት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በማሳወቅ፤ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ላይ አስፈላጊ የሚለውን እርምጃ ከመውሰድ አንስቶ ይሄንን ድርጊት በበላይነት የሚመሩ አመራሮችን በወንጀል እስከ መጠየቅ የሚያደርስ ህጋዊ መብት አለው ብለዋል፡፡

በማናቸውም ፍርድ ቤት የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ እንዳሉት “በህገ መንግስቱ ለፌደራልና ለክልል ተለይቶ የተሰጠ ስልጣን አለ ፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 50 ንዑስ አንቀፅ 8 ላይ ለፌደራል መንግስት የተሰጠ ስልጣን በክልሎች መከበር እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 102 ደግሞ ከማናቸውም ወገን ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ የምርጫ ህግን የማውጣትም ምርጫን የማስፈፀምም እውቅና ተሰጥቶት የተቋቋመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው” ብለዋል፡፡

የትራይ ክልላዊ መንግስት አመራሮች ለነዚህና ለሌሎች ተያያዥ ህጎች መገዛት እንዳለባቸው ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን መጣስ ፈልገው ነው ብለዋል::

በፌደራል በማናቸውም ፍርድ ቤት የህግ አማካሪና ጠበቃ እንዲሁም የህገ መንግስት ተማሪና ተመራማሪ የሆኑት ጠበቃ ነብዩ ምክሩ በአቶ ሽብሩ ሀሳብ ተስማምተው “ምርጫ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እየተተገበረ እንደሆነ መታየት አለበት” ያሉ ሲሆን “መቼ ያቋቋሙት ምርጫ ቦርድ ነው ይሄን የሚያየው፣ መቼስ ከመዘገቡት የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ነው የሚወዳደሩት” ብለዋል፡፡

የምርጫ ቁሳቁስ እንኳን ሲያዘጋጁ እንዳልነበር ያነሱት ጠበቃ ነብዩ ፖሊሲያቸውን እንኳን ለህዝቡ አላስተዋወቁም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ፤ አለም አቀፋዊ በሆነው ወረርሽኝ ምክንያት ይሄን ምርጫ ላካሂድ አልችልም እያለ ብቻዬን ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ እንቅስቃሴ መጀመር ህጋዊ ካለመሆኑም በላይ የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ መጣል ነው፡፡ የፌደራል መንግስትን በዚህ ደረጃ አለመታዘዝም ተገቢ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አዶናይ ሰይፉ በበኩላቸው በመሰረቱ ጉዳዩ “ህጋዊ ዋጋው የወደቀና የከሸፈ ሀሳብ ነው” ሲሉ ገልፀውታል፡፡

“የምርጫ ቦርድ እውቅና ያልሰጠውን ምርጫ አድርገው ፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ እንዴት ሊልኩ አስበው ነው?” ሲሉም ሀሳቡ “ህገ ወጥ ብቻ ሳይሆን ብስለት የጎደለው ጨዋታ ነው” ብለዋል፡፡

አቶ አዶናይ ሀሳቡ “ህገ መንግስቱን ብቻ ሳይሆን የምርጫ ህጉንም የሚጥስ ተግባር ስለሆነ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የምርጫ አዋጁ አንቀፅ 3 የተፈፃሚነቱን ወሰን ሲናገር ማንኛውም ህጋዊ ሰውነት ያለው አካል ከቦርዱ ፍቃድ ውጪ ምርጫ ሲያስፈፅም፣ የምርጫ ቁሳቁስ ሲያትምና ሲያባዛ ከተገኘ በወንጀል ይጠየቃል ይላል፡፡ ስለዚህ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ህጋዊ ሰውነት እንዳለው አካል በወንጀል ሊያስጠይቀው የሚያስችለውን ተግባር ነው ለመፈፀም ያሰበው ብለዋል፡፡

አቶ ሽብሩ ደግሞ ፌደራል መንግስት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ ካገኘ በኋላ አስፈላጊ የሚለውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በህገ መንግስቱ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ማፍረሱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አይቶ ካረጋገጠ በኋላ ፌደራል መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትሩና በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል አስፈላጊና ተገቢ ያለውን እርምጃ መውሰድ ይችላል ብለዋል፡፡

አቶ ነብዩ በበኩላቸው የፌደራል መንግስት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ህገ መንግስቱ ተጥሷል ሲል ጣልቃ ለመግባት ፍቃድ ይጠይቃል፣ ፍዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስቱ መጣሱን አረጋግጦ ይወስንና ለፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባና እርምጃ እንዲወስድ ፍቃድና ትዕዛዝ ይሰጣል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ነብዩ ገለጻ ከሆነ ደግሞ “ፌደራል መንግስት የሚወስደው እርምጃ መጠን ግን እንደ ህገ ወጥነቱ መጠን የሚወሰንና የሚለያይ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ህወሀት በበኩሏ እንደ ትግራይ ክልላዊ መንግስት በክልል ደረጃ ምርጫ እናካሂዳለን ማለታችን እንደውም ለሕገመንግስቱ ተገዥ መሆናችንን የሚያሳይ ነው ፤ ምርጫው ምርጫ ቦርድንም ባሳተፈ ሁኔታ ህጋዊ አፈፃፀም እንዲኖረው ይደረጋል እያለች ነው፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *