የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወሬና ተግባር እንዴት እየሄዱ ነዉ?

በአሁኑ ወቅትስ በአንድ ክፍል ዉስጥ እስከ 45 እና 90 ሰዎች በአንድ ላይ የሚሰሩባቸዉ ቢሮዎች አሉ ቢባሉስ ምን ይላሉ?

መነሻዉን ቻይና ዉሃን አድርጎ ድንገት የተከሰተዉና ዓለምን በማናወጥ ላይ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ሀገራትን በተለያየ መልኩ መፈታተኑን ቀጥሏል፡፡

ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየፈጠረ የሚገኘዉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ፣እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አልሆነም፤ወረርሽኙን በተመለከተ እየወጡ ያሉ መረጃዎች በቀጣይም ሊያደርሰዉ የሚችለዉ ተጽዕኖዉ ሲገለጽ ገና ምን ታየና የሚያስብል አዝማሚያ ያለዉ ነዉ፡፡

ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንዲሉ አበዉ፤ኢትዮጵያ ቫይረሱ ከመግባቱ አስቀድሞ መጠነኛ ግንዛቤ ፈጠራን፣ከገባ በኋላ ደግሞ የተለያዩ የመከላከያ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች፡፡

ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ደግሞ ሰራተኞች ስራቸዉን ከቤት ሆነዉ መስራት ከቻሉ፣ቢሮ አይምጡ፣ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም የግድ ካልሆነባችሁ በስተቀር በቤታችሁ መሽጉ ተብለን ነበር፡፡

ዳሩ የወረርሽኙ ስርጭት እየጨመረ ቢሆንም ብዝዎቻችን ግን ዋል አደር እያለን በመቸገርም ይሁን መዘናጋት ከቤታችን እየወጣን ለራሳችንም ለሌሎችም ስጋትን እየፈጠርን እንገኛለን፡፡

አንዳንድ መስሪያ ቤቶችም ቢሆን ከዚህ መሰል ቅሬታዎች አላመለጡም፡፡ ከፍተኛ ተገልጋዮችን የሚያስተናግደዉ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ደግሞ ከነዚህ ዉስጥ የሚጠቀስ ሲሆን ተዘዋዉረን በተመለከትንበት ጊዜም በርካታ ሰራተኞች ወደ ስራ እየገቡ መሆኑን ስንታዘብ፤የደረሱን ቅሬታዎች ደግሞ በአንድ ቢሮ እስከ 90 ሰራተኞች እንድንሰራ እየተደረግን ነዉ የሚል ነዉ፡፡

በኋላ መፍትሄ ሲባል ደግሞ 45 ሰዎች በአንድ ክፍል ዉስጥ እንዲሰሩ መደረጋቸዉን ነግረዉናል፡፡

ይህ ለምን ሆነ ስንል ጥያቄ ያቀረብንለት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በኮሙኒካሽን አስተባባሪዉ አቶ በላይነህ ወልደ-ሰንበት በኩል በሰጠዉ ምላሽ።

ሰራተኞችን በሽፍትና በቤታቸዉ ሆነዉ እንዲሰሩ እያደረግን ነዉ፣ ለአብንትም በወረዳ ደረጃ 75 በመቶ ሰራተኞቹ ቤታቸዉ ሆነዉ እንዲሰሩ፤በክፍለ ከተማ ደረጃ ደግሞ ሰራተኞቹ በሶስት ሽፍት እንድገቡ ይህም 65 በመቶ ሰራተኞች ቤታችዉ ሆነዉ ቀሪዎች ቢሮ ገብተዉ ስራቸዉን እንዲያከናዉኑ ነዉ እያደረግን ያለነዉ ካሉ በኋላ በተለይ ተገልጋይ የሚበዛባቸዉ የስራ መደቦች ግን እዉነት ነዉ በርከት ያሉ ስራተኞች እንዲገቡ እየተደረጉ ነዉ ብለዉናል፡፡

ሰራተኞቹ ብቻም ሳይሆን ወደ ቢሮዉ ጉዳይ ለማስፈጸም የሚመጡ ሰዎችም በቁጥር በዙ በመሆናቸዉ፣ደንበኞቹ በስማቸዉ ቅደም ተከተል ብቻ የሚስተናገዱበትን ጊዜ ለይተን አካላዊ ቅርርብ እንዳይፈጠር ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነዉ ብለዋል፡፡

ቢሮዉ ለሰራተኞቹ ቀደም ሲል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሲሰራ መቆየቱንና፣በአሁኑ ወቅትም ተራተኞቹ አልኮል፣ሳኒታይዘርና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንዲያገኙ ማድረጉን አስታዉሶ፣ከሰራተኞቹ ባሻገር እርዳታዉ ለሌላዉ የህብረተሰብ ክፍል እንዲደርስ ለማድረግም ለከተማ አስተዳደሩ 17 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አድረጉን አስታዉቋል፡፡

በዚህ ወቅት በየትኛዉም አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ብንሆን ግን መረሳት የሌለበት ጉዳይ ቅድሚያ ለደህንነታችን ትኩረት መስጠት ነዉ!!!

በሙሉቀን አሰፋ
ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.