የደቡብ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎችን ተላልፈዋል ባላቸዉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መዉሰዱን አስታዉቋል፡፡

የክልሉ ኮሙኒካሽን ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣዉን አዋጅ በመተላለፍ በሚምቀሳቀሱ የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነዉ ብለዋል፡፡

በአዋጁ የተጣሉ ክልከላዎች ስለመተግበራቸዉ በተደረገ ፍተሻም 176 የንግድ ተቋማት ክልከላዎችን ተላልፈዉ በመገኘታቸዉ እርምጃ እንደተወሰደባቸዉ ነዉ ሃላፊዋ የተናገሩት፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸዉ የንግድ ተቋማት መካከልም ሽሻና ጫት ቤቶች፣የምሽት መዝናኛ ቤቶች እንዲሁም ምርትን በመደበቅና ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ በማድረግ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ሱቆችና የእህል መሸጫ መደብሮች ይገኙባቸዋል ተብሏል፡፡

በተቋማቱ ላይም ከገንዘብ መቀጮ እስከ ማሸግና የንግድ ፈቃድ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን ወ/ሮ ሰናይት ነግረዉናል፡፡

በእነዚህ ድርጊቶች ላይ የተሳተፋና ሌሎች የአዋጁን ክልከላዎች ተላልፈዉ የተገኙ 141 ግለሰቦችም ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉ ነዉ የተነገረዉ፡፡

እስካሁን በወጡ መረጃዎች በክልሉ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ስድስት ሰዎች ናቸዉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እንደሚስተዋል የተናገሩት ሃላፊዋ፣ክልሉ የጤና ባለሙያዎችን፣የሃይማኖት አባቶችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በማስተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታዉቋል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልም ከህብረሰተቡ ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ነዉ የተባለዉ፡፡

የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል የኮሮና ቫይረስ ምርመራን እያከናወነ ሲሆን፣ኢንስቲትዩቱ በቀን እስከ 96 ሰዎችን ይመረምራል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሙሉቀን አሰፋ
ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.