የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ሰዎች እርቀታቸውን እንዲጠብቁ መልዕክት ሲያስተላልፉ እና ህግ ሲያወጡ ቆይተው ያንኑ ህግ ግን ሰዎች አብረዋቸው ፎቶ እንዲነሱ በመፍቀድ ሲጥሱ ታይተዋል በሚል ትችት እየቀረበባቸው ይገኛል፡፡
በማህበራዊ የትስስር ገፅ የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው ሁለት ሴቶች አብረዋቸው ፎቶ እንዲነሱ ሲጠይቋቸው ሲፈቅዱ እና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ በሚለው መመሪያ ላይ ሲያፌዙ ተስተውለዋልም ነው የተባለው፡፡
ፕሬዝዳንቱም “ከመታሰራችን በፊት ቶሎ ፎቶውን እንነሳ ለነገሩ ከናንተ ጋር ብታሰርም አይቆጨኝም“ ሲሉ መቀለዳቸውም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ባሳለፍነው እሁድ ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛውን የሚባል የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ቁጥር አስመዝግባለች፡፡
ይህም ቁጥር 1ሺ 160 ሲሆን ሀገሪቱ እስካሁን ካስመዘገበችው እለታዊ ሪፖርት ከፍተኛው ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ደቡብ አፍሪካ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ በሲጋራ እና መጠጥ ላይ እገዳ ከመጣል ጀምሮ ከበድ ያሉ ገደቦችን ካስቀመጡ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ነች ሲል ቢቢሲ በዘገባው ጠቅሷል፡፡
በአፍሪካ ከፍተኛው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ የሚገኝባት ሀገሪቱ እስካሁን 16 ሺ 433 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ሪፖርት አድርጋለች፡፡ 286 ሰዎችም በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በትግስት ዘላለም
ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም











