መንግስት ከደምቢ-ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በታገቱ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ሊከሰስ ነው።

የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ ባልታወቁ ሰዎች ከታገቱ 6 ወር ሊሞላቸው ጥቂት ቀናት ይቀራሉ።

ታዲያ እስካሁን የተፈጠረውን ነገር ይህ ነው ያለ እና በጉዳዩ ላይ የተሰራውን ስራ ያሳወቀ አንድም አካል የለም፡፡

መንግስት በጉዳዩ ላይ የሰጣቸው መግለጫዎች እንዲሁም ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው በሚልም በርካቶች ወቀሳ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡

አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት የተማሪዎቹ ጉዳይ እንዲዘነጋ በር ከፍቷል የሚሉ አሉ።

የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው
መንግስት በታገቱ ተማሪዎች ዙሪያ በቂ መረጃ እየሰጠን አይደለም ብለዋል።

የማህበር ስራ አስፈፃሚ ሌንሳ ቢየናም መንግስት ጉዳዩ ስለመከሰቱ በይፋ ካመነ ወዲህ የተማሪዎቹን ወላጆች ከማነጋገር ጀምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ጀምረን ነበር ብለዋል፡፡

የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላትን የጠየቅን ቢሆንም ይሄ ነው የሚል ምላሸ ማግኘት ግን አልቻልንም ብለዋል፡፡በመሀል ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ወደኋላ ጎትቶናል ብለውናል፡

በወቅቱ የተማሪዎቹ ወላጆች ልጆቻቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ሲነግሩን በማህበራዊ ትስስር ገፆች ሳይቀር ጫና ለመፍጠር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ጀምረን የነበረ ቢሆንም ይወጡ የነበሩ መረጃዎች ግልፅ አለመሆናቸው እንደ ማህበር ብዙ እንዳንጓዝ እንቅፋት ከሆኑብን ምክንያች መካከል ተጠቃሹ ነውም ይላሉ ስራ አስፈፃሚዋ፡፡

መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ ስላለበት በቂ ምላሽ እንዲሁም መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል የሚሉት የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ሌንሳ መንግስት ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን ጉዳዩ በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ ጫና እናደርጋለን ይህ ጫናም መንግስትን እስከ መክሰስ ይደርሳልም ብለውናል፡፡

በማህበራዊ የትስስር ገፅ የጀመርነው እንቅስቃሴ ይቀጥላል ነገር ግን ደግሞ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተስተጓጎሉ እንቅስቃዎች ወደ ነበሩበት መመለስ ሲጀምሩ የተማሪዎቹ ጉዳይ ላይ እንደ አዲስ ጫና መፍጠሩን እንቀጥላለንም ብለውናል፡፡

እንደ ዜጋ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለተማሪዎቹ ድምፅ ሊሆን ይገባል የሚሉት ስራ አስፈፃሚዋ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የመፍትሄ አካል ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

የሲቪሉ ማህበረሰብም ቢሆን የተማሪዎቹን ጉዳይ እንደ አንድ ሰብአዊ መብት ጥሰት ተመልክተው ጫና መፍጠሩ ላይ አብረውን እንዲሰሩ እንፈልጋለንም ሲሉም ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በትግስት ዘላለም
ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *