የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የገጠመዉ ችግር ምንድን ነዉ?

የተሰበሰበዉን ገንዘብ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች ሀሰት ናቸዉ ሲል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ገልጿል፡፡

‹‹በቀን አንድ ዶላር›› በማዋጣት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ድጋፍ እንዲሰጡ በተጠየቀዉ መሰረት ትረስት ፈንዱ ከዳያስፖራዉ ሕብረተሰብ 25 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ለጋሾች 6 ነጥብ 36 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡን ገልጧል፡፡

በዚህም በትረስት ፈንዱ የምዘና መስፈርት ለገንዘብ ድጋፍ ብቁ የሆኑ አምስት ፕሮጀክቶች ተመርጠዉ ከድርጅቶቹ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አስታዉቋል፡፡ 17 ፕሮጀክቶች ደግሞ መመዘኛዎችን እያሟሉ በሂደት ላይ ናቸዉ ብሏል፡፡

ትረስት ፈንዱ አክሎም፣ለጤና ባለሙያዎች መከላከያ የሚውሉ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች፣ የፊት መከለያዎች፣ የመከላከያ አልባሳትና የመተንፈሻ መሣሪዎች የተካተቱበት ከ1 ነጥብ 37 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ ለጤና ሚኒስቴር ለማስረከብ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጦ፣ከዚህ ዉጭ ግን ምንም አይነት ገንዘብ ወጭ አልተደረገም ሲል ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ግን በትረስት ፈንዱ የተሰበሰበዉ ገንዘብ አላግባብ ጥቅም ላይ ሊዉል የሚችልበት አግባብ እንዳለ በማስመሰል በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መሰራጨቱ አሳዝኖኛል ነዉ ያለዉ፡፡ትረስት ፈንዱ ይህን ይበል እንጂ፤

ሪፖርተር ጋዜጣ የአማርኛ ክፍል በግንቦት 9 እትሙ፣የኢትየጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ፣ በቦርድ አመራሮች ውዝግብ የህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል መባሉን ዘግቦ ነበር፡፡

ዉስግቡ የጀመረው ደግሞ ካሰባሰው የ6.36 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ አምስት ሚሊዮን ዶላር በመመደብ፣ ከ22 ፕሮጀክቶች ውስጥ ለአምስቱ ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት ካደረገ በኋላ ተፈጠሩ በተባሉ የሥነ ምግባርና ሌሎችም ከአሠራር ያፈነገጡ ተግባራት ጋር በተያያዘ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በመግለጽ ደብዳቤ እንደጻፋ ይገልጻል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ እንደሚለዉ ዉዝግቡ ውስጥ ውስጡን የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግባቸው ከቀረቡት ፕሮጀክቶችና ውድቅ ከተደረጉት ጋር እንደሚያያዝ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ማሳወቃቸዉን ይገልጻል፡፡

እነዚህን ጉዳዮች ሁሉ ይዘን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማጣራት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የኮሙንካሽን ባለሙያ ወደ ሆኑት ሃና አጥናፋ በተደጋጋሚ ብንደዉልም ምላሻቸዉን ማግኘት አልቻልንም፡፡

በሙሉቀን አሰፋ
ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *