ግብጽ ከቱርክ ጋር ወደ ጦርነት ልታመራ እንደምትችል ተገለጸ።

ግብጽን ለ30 ዓመታት የመሩት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ሆስኒ ሙባረክ በህዝባዊ አመጽ ከስልጣናቸቨው መነሳታቸውን ተከትሎ ቱርክ የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ወደ ስልጣን እንዲመጡ ትልቅ ድጋፍ ስታደርግ ነበር።

ሙሃመድ ሙርሲ ወደ ስልጣን በመምጣታቸውን ቱርክ ለግብጽ ድጋፍ ስታደርግ የነበረ ቢሆንም አብደል ፋታህ አልሲሲ የሙርሲን ስልጣን ቀምተው ወደ ስልጣን ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የግብጽ እና ቱርክ ወዳጅነት ወደ ከፋ ሁኔታ ተሸጋግሯል።

በሊቢያ በመንግስታቱ ድርጅት የሚደገፈው የፈይሰል አል ሲራጅ መንግስት እና እራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ዘብ ነኝ እያለ በሚጠራው በኮማንደር ከሊፋ ሀፍታር ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ ሁለቱ አገራት የጥቅም ግጭት ተከስቷል።

ሁለቱ አገራት ቱርክ የሊቢያን መንግስት ስትደግፍ ግብጽ ደግሞ ከሊፋ ሀፍታርን በመደገፏ ምክንያት የእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ ናቸው።

በምስራቃዊ ሜዲትራኒያን ባህር ላይም ሁለቱ አገራት በባህር ሃይል መፋጠጣቸውን ቀጥለዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ካሉ አስላመዊ ሀገራት መካከል የ50 በመቶውን ህዝብ ብዛት የያዙት ግብጽ እና ቱርክ ከሚያወዳጃቸው ጉዳዮች ይልቅ የሚፋጠጡባቸው አጀንዳዎች እየበዙ ናቸው።

በቱርክ ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴ የደህንነት ስጋት የገባት ግብጽ የብሔራዊ ደህንነት አደጋዎችን ለመቀልበስ በየትኛውም ስፍራ ጥቃት ለማድረስ መዘጋጀቷንም አስታውቃለች፡፡

ግብፅ በብሔራዊ ደህንነቷ ላይ የሚደርሰውን ስጋት እንደማትታገስ የገለፀች ሲሆን ይህንን ለመከላከል አስፈላጊውን የአፀፋ እርምጃ እንደምትወስድ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለዴሊ ኒውስ ኢጂፕት ተናግረዋል፡፡

የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ትናንት ቱርክ በሶሪያ እና በሊቢያ ከሚገኙ አልቃይዳን ከመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች ጋር ተባባሪ መሆኗ ያስከተለውን ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ገምግመዋል፡፡

ከስብሰባው በፊት የሀገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ሙሀመድ ዛኪ እንዳሉት ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ የግብፅ ጦር አዛዦች የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ እንደተናገሩት ግብፅ ማናቸውንም አሸባሪ ቡድኖችንም ሆነ ደጋፊዎቻቸውን አትታገስም ያሉ ሲሆን ሊቢያ የግብፅ ብሔራዊ ደህንነት አካል ናት ሲሉ ተደምጠዋል ተብሏል፡፡

በግምገማውም በሀገሪቱም ሆነ በሌላ ቀጠናዊ ቦታዎች ላይ ያሉ ስጋቶችን ለመቀነስ አስፈላጊውን አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል ሲሉ በስብሰባው ላይ ታድመው የነበሩት ከፍተኛ ባለስልጣኑ ተናግረዋል፡፡

ትናንት በተካካሄደው ውይይት ከተገኙ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የጦር ኃይሎች ኦፕሬሽን ባለሥልጣን ፣ የጦር ኃይሎች ኢንጂነሪንግ ባለሥልጣን እንዲሁም የማዕከላዊ ወታደራዊ ክልል አዛዥ ይገኙበታል ተብሏል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በደረሰ አማረ
ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *