በትግራይ እየተካሄደ ያለው የወጣቶች አመጽ የህወሃት አመራሮች የጥቅም ሰንሰለት የፈጠረው ችግር መሆኑን አረና አስታወቀ።

በክልሉ እየተካሄደ ያለው ይሄንን አመጽ ፓርቲው እንደሚደግፈውም አስታውቋል።

የኮሮና ቫይረስ መከሰት በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የማስከተሉን ያክል የፖለቲካውን አለም መልክም በከፊል ቀይሮት ቆይቷል፡፡

ሃገራችን በተለያዩ ጎራዎች በተሰለፉ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች እየተናጠች በነበረችበት ቅድመ- ኮሮና ዘመን ፤ በአንጻራዊነት ሰላም የሰፈነባት ክልል ነበረች፤ትግራይ፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ክልሉን የሚመራው ፓርቲ አምባገነንነት ነው የሚለውን መከራከሪያ የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።

ከሰሞኑ ታዲያ በእለታዊው ኮሮና ሪፖርት ቁጥሮች በአስፈሪ ፍጥነት ከፍ እያሉ ባሉበት በዚህ ሰዓት ፤ በርከት ያሉ የትግራይ ወረዳዎች በክልሉ መንግስት ላይ መረር ያለ ተቃውሞን እያሰሙ ነው፡፡

የአረና ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት አቶ አምዶም ገ/ስላሴ በዋናነት በጥቅምና ትውውቅ ትስስር ላይ ተመሰረተው የህወሃት ሹመት የፈጠረው ቁጣ ነው ይላሉ፡፡

በየወረዳዎቹ ተሹመው የተላኩት ግለሰቦች በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን ካለማግኘታቸው በተጨማሪ ፤ጊዜውን ጠብቆ የማሟያ ምርጫ ሳይካሄድ የመጡ በመሆናቸው ሹመታቸውም ህገ መንግስቱን የጣሰ ነው ነው የሚሉት፤ተቃውሞው ከህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ የህወሃት ካድሬዎች ጭምር እየተሰማ መሆኑን አንስተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በሚል ፖሊስ በወሰደው እርማጃ 3 ሰዎችን በጥይት መምታታቸውን የሚያስታውሱት አቶ አምዶም በዚህም ሳቢያ መቀሌ ላይ ቁጣ መቀስቀሱን ነው የነገሩን፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት ባሁኑ ሰዓት ይህን በትስስር የተዘረጋውን ኔትዎርክ የሚቃዎሙ የህወሃት አባላት ላይም ድርጅቱ ማባበያም ማስፈራሪያም እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡ህወሃት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን ሊያካትት ይገባል የሚሉት አቶ አምዶም አረና እንደ ፓርቲ የህዝቡን ጥያቄ ትክክለኛነት በማመን ድጋፉን ይሰጣል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ዜጎች በመንግስት ላይ ተቃውሞ ማሰማት ከጀመሩ አንድ ሳምንት አልፏል፡፡የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለመጠይቅ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሃብቶቻቸው ብዝበዛና ውድመት መኖሩን አንስተዋል።

እነዚህ የተፈጥሮ ሃብታቸው የወደመባቸው ዜጎችም ፍትህና ካሳ እየጠየቁ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በለስ ላይ የደረሰው ውድመት ሆን ተብሎ የአንዳንድ አካባቢዎች የኢኮኖሚ አቅም ለመጉዳት የተፈጠረ ነው የሚል እምነት እንዳለም ነው አቶ ነብዩ የተናገሩት፡፡

ከአላማጣ እስከ ዛላምበሳ በሚገኝ የበለስ ተክል ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱን በማሳያነት አንስተዋል።

ህወሃት በበኩሉ በትግራይ የሚካሄድ ምንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ የለም እንዲሁም ሰሞኑን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ትግራይን አስመልክቶ እየዘገቡት ያለው ሁነት ፈጽሞ ውሸት ነው ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ።

https://t.me/ethiofm107dot8

በአባይነሽ ሽባባውግንቦት

17 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *