የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬት ወስደው በሚገባ ያላለሙ 20 ኢንቨስተሮችን መሬት መቀማቱን አስታወቀ።

የክልሉ የአካባቢ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታ ሃይሉ እንዳሉት በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን የስራ እንቅስቃሴ በመገምገም የወሰዱትን መሬት ሳያለሙ በተገኙ 18 የእርሻና 2 በእጣን ማምረት የተሰማሩ የኢንቨስትመንት ባለሃብቶች ፈቃድና የመሬት ውላቸው ተሰርዟል።

በክልሉ 103 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው ውል በመግባት 8 ሺህ 376 ሄክታር መሬት በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፉ ተሰማርተዋል።

ይሁንና እነዚህ ባለሃብቶች መሬቱን ባለማልማታቸው ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓልም ብለዋል።

ይህ መሬትም በቀጣይ የማልማት አቅም ላላቸውና መስፈርቱን አሟልተው ለሚቀርቡ ባለሃብቶች እንደሚሰጡም ሃላፊው ገልጸዋል።

11 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ በቀጣይ በገቡት ውል መሰረት የታዩባቸውን ክፍተቶች በመቅረፍ እንዲያለሙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።ባለፉት ዓመታት እርምጃ በተወሰደባቸው 13 ፕሮጀክቶች ተይዞ የነበረው 5 ሺህ 385 ሄክታር መሬት በባንክ እዳ ተይዞ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ በባንክ ዕዳ ተይዞ የነበረውን መሬት ጨምሮ 10 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ላላቸው ባለሃብቶች ለመስጠት ክልሉ ዝግጁ ማድረጉንም ኃላፊው ገልጸዋል ፡፡

ቢሮው በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ለሃገር እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ክልሉ ከ56 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።በመሆኑም የማልማት አቅም ያላቸው ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ።

https://t.me/ethiofm107dot8

በደረሰ አማረ

ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.