የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት እና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል እንደሚደግፍ አብን አስታወቀ።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት እና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል እንደሚደግፍ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የትግራይና የአማራ ሕዝብ ለዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት አላቸው ህዝቦች ናቸው ያለው አብን “ትሕነግ” ባለው በህወሓት ሲራመድ በነበረው ስርዓት ምክንያት የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ፈተና ላይ ወድቆ ቆይቷል ብሏል።

ሕወኃት በአገራችን በልዩ ሁኔታ ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ በጥላቻ ተመስርቶ ሥራ ላይ ባዋለው ሕገ መንግሥትና ልዩ ልዩ ፖሊሲዎች የአገራችንን አንድነት እና ሉአላዊነት አደጋ ላይ የጣለ፣ መላዉ የአገራችን ሕዝብ በተለይም የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ ረፍት እንዳያገኝ አገር የማተራመስ ፖሊሲ የሚያራምድ ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይል መሆኑን ንቅናቄው በመግለጫው አስታውቋል።

ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከተሸነፈ በኋላ በትግራይ ሕዝብ መካከል መሽጎ የጥፋት እና የሴራ መረቡን በመዘርጋት ዛሬም እንደለመደው ለትግራይ ህዝቦች አማራ ጠላት መሆኑን መናገሩን ቀጥሎበታል ብሏል።

በኢትዮጵያ በየቦታው በሚካሄዱ የጥፋት ጥቃቶች ጀርባ ትህነግ እጁ አለበት አሁንም የትግራይ ወጣቶች ለነጻነት ሲወጡ ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ አፈና መፈጸሙን ቀጥሏል ብሏል።

በትህነግ አገዛዝ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ለደረሱ የክፋት ስራዎች ሁሉ ተጠያቂው ይሄው ድርጅት እንጂ የትግራይ ህዝብ አለመሆኑን የአብን ዕምነት መሆኑንም አስታውቋል።

የትግራይ ሕዝብ ራሱን በመንደር እና በጎጥ አደራጅቶ እያጠቃው ካለው የትሕነግ አገዛዝ ጋር የሚያደርገውን ትግል አብን፣ የአማራ ሕዝብ እና መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በትኩረት እየተከታተልን መሆኑን ይወቅልኝ ብሏል።ንቅናቄው ከአራት ኪሎ የተባረረው የሕውኃት-ትሕነግ መንኮታኮት ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ብቻ መሆኑን ተረድቶ የትግራይ ህዝብ አገዛዙን ለመገርሰስ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል።

የትግራይ ሕዝብ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት መካከል ደንቃራ የሆነውን የተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን፤ የትሕነግ የአገዛዝ ስርዓት ከራሱ ላይ አሽቀንጥሮ በመጣል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቹ ጋር በአንድነት ለመቆም፤ ለፍትኅ፣ ለእኩልነትና ለነጻነት በሚያደርገው ትግል አብን ከጎኑ እንደሚቆም አስታውቋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ።

https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም

የኢትዮጵያዊያን

ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *