ቻይና የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ከ6 ወራት በኋላ ለዓለም ማሰራጨት እንደምትጀምር አስታወቀች።

የቤጂንግ ባዮሎጂካል ምርምር ኢንስቲትዩትና የቻይና ብሔራዊ ባዮቲክ ቡድን በጋራ እያዘጋጁት የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ክትባት 2 የምርመራ ፈተናዎችን አጠናቆ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ለገበያ ዝግጁ ሊሆን እንደሚችል ብሉምበርግ ዘግቧል።

ቻይና የኮሮና ቫይረስ ክትባት በዚህ አመት በስፋት ለማምረት ዝግጅት እያከናወነች ሲሆን በየአመቱ ከ 100 ሚሊዮን እስከ 120 ሚሊዮን ክትባቶችን የማምረት አቅም ይኖራታል ተብሏል።

መድሀኒት ቀማሚዎች እስካሁን ቢያንስ 365 ሺህ ሰዎችን ለገደለው ተላላፊ በሽታ መድኃኒት ለማግኘት እየጣሩ ነው።

በዓለም ዙሪያ ከ 100 በላይ የሚሆኑ የቫይረሱ ክትባቶች በላብራቶሪዎች እየዳበሩ ይገኛል።

ይሁን እንጂ በጣም ወሳኝና የመጨረሻውን የሰው ክሊኒካል ሙከራ ማለፍ የቻሉት ጥቂቶች ናቸው።

በአጠቃላይ በቻይና ኩባንያዎች አምስት ክትባቶች በሰው ልጆች ላይ ሙከራ እየተደረገባቸው ሲሆን እነዚህን በስፋት በማምረት በየትኛውም ሀገር ለማሰራጨት ጥረት ይደረጋል ተብሏል።

በቻይና ሳይንቲስቶች እየተዘጋጀ የሚገኙትን ክትባቶች ወደ ምርት ለማስገባት የሚያስችል ተግባራት በቻይና መንግስት እየተደገፉ ነው።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ ማንኛውንም የተሳካ ክትባት ለዓለም ለማጋራት ቃል ገብተዋል።

የቻይና የመድሀኒት ኩባንያዎች አሁንም በርካታ ውጣውረዶችን በመጋፈጥ ላይ ሲሆኑ ፈዋሽ ክትባቱን ቀድሞ በማግኘት ዓለምን መካስ እንደሚፈልጉ በመናገር ላይ ናቸው፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በደረሰ አማረ
ግንቦት 22 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.