በሶማሌ ክልል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ልጆች ከመጻህፍት እንዳይለዩ የግመል ቤተ መጻህፍት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የህጻናት አድን ድርጅት አስታወቀ፡፡

የሴቭ ዘ ቺልድረን ኮምዩኒኬሽን ሃላፊና ቃል አቀባይ ወ/ሮ ህይወት እምሻው ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለጹት በሶማሌ ክልል ተንቀሳቃሽ የግመል ቤተ መጻህፍት አገልግሎት መስጠት የተጀመረው ከአስር አመታት በፊት በ21 ግመሎች ሲሆን፤ በዚህ ሰዓት በመቶዎች የሚቆጠሩ ግመሎት በዚህ አገልግሎት ላይ ተሰማርተዋል፡፡

ሃገሪቷ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ባሳለፈቻቸው ውሳኔዎች መሰረት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መለዬታቸውን ተከትሎ፤ በክልሉ በ33 መንደሮች የሚገኙ የአርብቶ አደር ልጆች በርከት ያሉ መጻህፍትን እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለውናል፡፡

እያንዳንዱ ግመል እስከ 200 መጻህፍትን በአንዴ የመያዝ አቅም እንዳላቸው የነገሩን ወ/ሮ ህይወት፤ መጻህፍቱን ለህጻናቱ በሚደርሱበት ወቅትም የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይኖር ጥንቃቄ እንደሚደረግ ነግረውናል፡፡

የመጻህፍቱ ይዘትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተጻፉ እድሜያቸውን የሚመጥኑና የንባብ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩ መሆናቸውን ነው የነገሩን፡፡

ድርጅቱ ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ አልፎ አልፎ መቀዛቀዞች ቢኖሩም በአፋር ክልልና በሌሎች የሃገሪቷ ክፍሎችም አህያን በመጠቀም የተንቀሳቃሽ ቤተ መጻህፍት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ወ/ሮ ህይወት ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በአባይነሽ ሽባባው
ግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *