ፔፕሲኮ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ለተጎዱ እና ጫና ለደረሰባቸው ዜጎች 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ለገሰ።

ፋውዴሽኑ ይህንን ድጋፍ የሚሰጠው ከሜቄዶንያ አረጋዊያን መርጃ ማህበር ጋር በመተባበር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ጫና በስፋት ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ አካላትን ለመደገፍ መሆኑን ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሥጋት እና የንግድ እንቅስቃሴ ገደብ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡

ለዚህ ዓለም አቀፋዊ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም ፔፕሲኮ ከታወቁ ግብረሰናይ ተቋማት ጋር በመጣመር በይበልጥ ጫናው ክንዱን ላሳረፈባቸው አካላት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ይህ ድጋፍ ምግብይለግሱተስፋንይቀጥሉ ፕሮግራም አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን በመደገፍ ከሚታወቀው ሀገራዊ የበጎ አድራጎት ተቋም መቄዶንያ ጋር በጥምረት የሚከናወን ነው ተብሏል፡፡

ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የፔፕሲኮ መጠጦች ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሰርጂኦ ፓያ “ምግብ ይለግሱ – ተስፋን ይቀጥሉ የተሰኘውን ፕሮግራም የቀረጽነው በወረርሽኙ ሳብያ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የማኅበረሰብ አካላት በአስፈላጊ ድጋፎች ለመድረስ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ውስጥ ካሉ የምግብ እና የመጠጥ አምራቾች አንዱ እና ግንባር ቀደም የሆነው ድርጅታችን በወረርሽኙ ምክንያት ለተጎዱ አካላት የምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ያምናል፡፡” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የምግብ እርዳታ ለሚሹ አካላት ድጋፍ በማድረግ ለማኅበረሰባችን መድረስ እንዳለብን አናምናለን፡፡” ብለዋል፡፡

የመቄዶንያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ብንያም በለጠም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የኢኮኖሚ ዐቅማቸው ደካማ በሆነ ኢትዮጵያውያን ላይ ምን ያህል ከባድ ጫና እንደሚያሳርፍ በሚገባ እንረዳለን ብለዋል።

በዚህ ድጋፍ አማካኝነትም ከ100 በላይ ለሆኑ ተከታይ ቀናት ለ2000 ሰዎች የምግብ ድጋፍ ለማድረግ እንችላለን፡፡” ብለዋል፡፡

የ#ምግብይለግሱተስፋንይቀጥሉ የድጋፍ ፕሮግራም የፔፕሲኮ ፋውንዴሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለተጎዱ አካላት ከሚያደርገው የ45ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡

ድርጅቱ ከምግብ ድጋፍ ባሻገርም ለጤና ባለሙያዎች አስፈላጊ የሆኑ የመጠበቂያ እና መከላከያ መሣሪያዎችን፣ የምርመራ አገልግሎት መስጫዎችን እንዲሁም ከ50 ሚሊየን በላይ ምግቦችን ከዓለም አቀፉ የምግብ ባንክ እና መሰል የበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዓለም ላሉ ሀገራት ለማሠራጨት ዝግጅቴን ጨርሻለሁ ብሏል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በአባይነሽ ሽባባው
ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *