በዳርፉር የሰብአዊ መበት ጥሰት የፈጸሙ የታጣቂዎች ቡድንን የመራው ሱዳናዊ በአለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው፡፡
አለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ትናንት እንዳስታወቀው የታጣቂ ቡድኑ መሪ አሊ ኩሻያብ በጦር ወንጀል እና ሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ ይመሰረትበታል፡፡
ግለሰቡ በማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
እንደ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ ኩሻያብ ለአለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፎ የተሰጠ የመጀመሪያው ሱዳናዊ ግለሰብ ነው፡፡
በፈረንጆቹ ከ2003 እስከ 2004 ድረስ በምእራባዊ ሱዳን በምትገኘው ዳርፉር፤ በአስገድዶ መድፈርና ግድያ ወንጀል ምርመራ ተከፍቶበት በ2007 የእስር ማዘዣም ወጥቶበት ነበር፡፡
ኩሻያብ መንግስትን በመቃወም በአካባቢው በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች 199 ሰዎችን ለሞት 40 ሺህ የሚሆኑትን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነው ታጣቂ ቡድን ዋና አዛዥ መሆኑን መርማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በሱዳን ዳርፉር በነበረው ግጭት 200 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ 2.5 ሚሊዬን የሚሆኑት ደግሞ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡
አሜሪካ ድርጊቱን የዘር ማጥፋት ብትለውም፤አለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ግን ኩሻይብን በዚህ ወንጀል ክስ አልመሰረተበትም፡፡
ሲጂቲኤን ከማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የመንግስት ሰዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ኩሻይብ በሰሜናዊ ቢራዎ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሎ በአውሮፕላን ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ወደሚዳኙበት ሄግ ከተማ ተወስዷል፡፡
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት ኦማር ሃሰን አል-በሽር በዳርፉር በተፈጸመው ዘር ማጥፋት፣የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የጦር ወንጀል በፍርድ ቤቱ ተፈላጊ ናቸው፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በአባይነሽ ሽባባው
ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም











