እስከ መጭዉ የገና በዓል ድረስ 10 ሚሊዮን እንግሊዛዊያን በኮሮና ቫይረስ ሊጠቁ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡

የሀገሪቱ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት ኤን ኤች ኤስ እንዳለዉ የቀጣዮቹ ሰባት እና ስምንት ወራት ለእንግሊዛዊያን እጅግ አስቸጋሪና አስከፊ የቀዉስ ወራት እንደሚሆኑ ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት ባለሙያዎች በከፍተኛ የስራ ብዛት መዳከማቸዉን የጠቀሰዉ ጥናቱ፣አንዳንዶቹ የጤና ተቋማት ያሏቸዉን መመርመሪያና የህክምና መርጃ መሳሪያዎች ሳይቀር አሟጠዉ ተጠቅመዉ በቀጣይ የሚሆነዉን እንዲሁ እየተጠባበቁ ይገኛሉ ነዉ ያለዉ፡፡

የቫይረሱ ስርጭት ለሁለተኛ ዙር ይከሰታል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳለዉ የገለጸዉ ተቋሙ፣በዚህም እስከ ቀጣዩ የገና በዓል ድረስ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሊጠቁ ይችላሉ ማለቱን ITV NEWS ዘግቧል፡፡

ይህም የሀገሪቱን የህክምና አገልግሎት አቅም በእጅጉ ከመፈታተኑም ባሻገር እንደ ካንሰር፣ስትሮክና የልብ ህመም ያለባቸዉና ትልቅ ትኩረት ሊያገኙ የሚገባቸዉ ታማሚዉች እንዲዘነጉ ሊያደርጋቸዉ ይችላል፤የመደበኛ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥንም እስከ 60 በመቶ እንዲቀንስ ያደርጋልም ነዉ ያለዉ፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ኒያል ዲክሶን፣በአሁኑ ወቅት የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እየተነሱና ሀገሪቱ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ እንድትመለስ እየተደረገ ቢሆንም በቀጣይ ስለሚያመጣዉ መዘዝ እየታሰበበት አለመሆኑ ስጋት እንዳሳደረባቸዉ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱ የፓርላማ አባል የሆኑት ጆናታን አስወርዝ፣መንግስት የጤና ተቋሙን የጥናት ሪፖርት በቸልታ እንዳይመለከተዉ መክረዋል፡፡

ግብዓት የሚያስፈልጋቸዉ የጤና ተቋማት ተለይተዉ በአፋጣኝ ግብዓት እንዲሟላላቸዉ እንዲደረግና የእንቅስቃሴ ገደቦች ሲነሱም በዛዉ ልክ የእንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ የሚደረጉበት አሰራር ሊመቻች ይገባል ብለዋል፡፡

በእንግሊዝ እስካሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች፣155ሽህ 600 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን 29 ሽህ 673 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ለህልፈተ-ህይወት ተዳርገዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሙሉቀን አሰፋ
ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *