በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረው የሶሰትዮሽ ውይይት በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ ቢሆንም በሕግ ጉዳዮች ላይ ግን አሁንም ችግር መኖሩን ሱዳን አስታወቀች።

ሱዳን የመጀመርያ ዙር ውሀ ሙሌት ላይ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ቴክኒካዊ ጉዳዪች መሻሻሎች እያታዩበት ቢሆንም ህጋዊ ጉዳዮች ገና ይቀሩታል ብላለች፡፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙርያ የሚደረገው ድርድር በቴክኒክ ረገድ መሻሻሎች አሳይቷል ህግ ነክ ጉዳዮች ግን ገና ይቀሩታል ያሉት የሱዳን የውሀ እና መስኖ ሚኒስትር ያሰር አባስ ናቸው፡፡

የግድቡ ደህንነት፣ስለመጀመርያው ዙር የውሀ ሙሌት፣የረጅም ጊዜ አጠቃቀሙ፣ የመረጃ ልውውጥ ፣አካባቢያዊ ጥናት እና የቴክኒክ ትብብር ኮሚቴ ላይ የተደረገው ድርድር በጉልህ የሚታይ መሻሻል አሳይቷል፣ህግ ነክ ጉዳዮች ግን ገና ይቀራሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለሚፈረመው ስምምነት ሀገራቱ የሚገቡት የህግ ግዴታ፣ የሚፈረመው ስምምነት አተገባበር፣ ስምምነቱ መሻሻል ካለበት የሚሻሻልበት መንገድ እየተነሱ ካሉ የህግ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

የሱዳን የውሀ እና መስኖ ሚኒስትርያሰር አባስ መግለጫ ሳምንት ከፈጀው በቪዲዮ ኮንፈረንስ ከተደረገው ስብሰባ በኋላ የተሰጠ ነው፡፡

ዛሬ በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረገው ስብሰባ የሚቀጥል ሲሆን ሁሉም ሀገራት የህግ ጉዳዮችን የሚያይ የየራሳቸው ቡድን ይዘው ይገኛሉ።

በአሜሪካ፣ በተመድ እና በአለም ባንክ ታዛቢነት በሶስቱ ሀገራት መካከል በዋሽንግተን ሲደረግ የነበረው ድርድር የካቲት ከተቋረጠ በኋላ በዚህ ወር ነው በድጋሚ የተጀመረው፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን ከሚያዋስናት ድንበር 25 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትሰራው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በመጪው ሀምሌና ነሐሴ ከሚዘንበው ዝናብ በመጀመርያ ዙር ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ከዩቢክ ሜትር ውሀ አገኛለሁ ብላ አቅዳለች፡፡

ይሄ የውሀ መጠን ደግሞ በ ፈረንጆቹ 2021 አጋማሽ ሁለት ተርባይኖችን ለመሞከር በቂ እንደሆነ አናዶሉ ዘግቧል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.