በ2012 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ለማግኘት የታቀደው ገቢ ሙሉ በሙሉ ላለመገኘቱ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች እንዱ የወጪ ንግድ ምርቶች አቅርቦት እጥረት ነው፡፡
በ2013 በጀት ዓመት የአቅርቦት መጠኑን በማሻሻል ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ ከዚህ በፊት ግብይታቸው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሚፈጸሙ የወጪ ንግድ ምርቶች በተጨማሪ ሦስት የግብርና ምርቶች ግብይታቸው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡
በህገ-ወጥ እና በኮንትሮባንድ እየባከኑ ያሉ የእርግብ አተር፣ ቀይ ዥንጉርጉር ቦሎቄ እና ፒንቶ ቢን የተባሉት ምርቶች ከመስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ግብይታቸው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ስርዓት ብቻ እንዲፈጸም መወሰኑን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በዚህም የተነሳ በ2011/12 ምርት ዘመን የተመረተና በበልግ የተመረተ ምርት በክምችት ያላቸው አቅራቢዎች፣ ጅምላ ነጋዴዎች እና ላኪዎች የ2012/13 ምርት ዘመን አዲስ ምርት ከመድረሱ በፊት እስከ መስከረም 30/2013 ዓ.ም ድረስ አቅራቢዎችና ጅምላ ነጋዴዎች ለላኪዎች ሸጠው ላኪዎች ደግሞ ወደ ውጪ ልከው እንዲያጠናቅቁ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የመጀመሪያ የግብይት ማዕከላት እንዲያዘጋጁ፣ህጋዊ አቅራቢዎች አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት ዝግጁ እንዲሆኑና ህገ-ወጥ የምርት ግብይትና ዝውውርን ለመቆጣጠር አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት እንዲደረግ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርቶቹን የኮንትራት ሰነድ፣ የምርት መቀበያ ማዕከላትና የገበያ መሰረተ-ልማቶች ከወዲሁ ዝግጅታቸው እንዲጠናቀቅም ሚኒስቴር መልዕክቱን አስተላልፏል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያውያን
ሐምሌ 13 ቀን 2012 ዓ.ም











