ኢትዮጵያ በ10 ቀናት ውስጥ 15 ሚሊዮን ህፃናትን የኩፍኝ ክትባት መከተቧን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

የከቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ህፃናትን በ 10 ቀናት ውስጥ የኩፍኝ ክትባት መከተቧን የአለም ጠየና ድርጅት በድረገጹ ገልጿል፡፡

ይህ ሀገር አቀፍ ዘመቻ ከአለም ጤና ድርጅት፣ከዩኒሴፍ፣ ታዳጊ ሀገራት ላይ አዳዲስ ክትባቶች እንዲተዋወቁና እንዲሻሻሉ ከሚሰራው Gavi, the Vaccine Alliance እና ከአሜሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል በተገኘው ድጋፍ ፤ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሪነት ተከናውኗል፡፡

ይሄ የክትባት ዘመቻ በመጀመርያ የታቀደው በሚያዚያ የነበረ ሲሆን፤ በኮቪድ 19 ምክንያት ለ ሀምሌ ስለተላለፈ ነው አሁን የተካሄደው፡፡

ዘመቻው ለአስር ቀናት የቆየውና ተመሳሳይ መጠን ካላቸው የክትባት ዘመቻዎች ሊረዝም የቻለው በሰው መጨናነቅ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን በኮሮና የመጠቃት ዕድል ለማስወገድ ነው ተብሏል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ክፍት በሆነ ቦታ የፊት መሸፈኛ ማስክ አድርገው ክትባቱን እንዳከናወኑ ተገልጧል፡፡

እንደ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እጅን በአግባቡ መታጠብ ፣ ሙቀት ልየታ ፣ እና የመሳሰሉት ለኮሮና የተቀመጡ መመርያዎች እንደተተገበሩ የአለም ጤና ድርጅት በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡

ከ ዘጠኝ እስከ ሀምሳ ዘጠኝ ወራት ያሉ ህፃናትን አላማ ባደረገው ክትባት ማህበረሰቡ ስለዘመቻው ግንዛቤ እንዲያገኝ ተደርጓል የተባለ ሲሆን ክትባቱን ማከናወኛና ራስን መጠበቂያ እንዲሁም ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በመርከብ ተጓጉዘው በየቦታው እንደደረሱ ተገልጧል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት እንዳሳወቀው ዘመቻው 15 ሚሊዮን ህፃናትን ለመከተብ የነበረ ሲሆን 14.4 ሚሊዮን በመከተብ 96 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡

ይሄ የሚያሳየው ከኮቪድ 19 ጋር ከምናደርገው ትግል ጎን ለጎን ሀገራት ህይወት አድን ክትባቶችን ማድረግ እንደሚችሉ ነው ሲል ገልጧል፡፡

የአለም ጤና ድርጀት የአፍሪካ ክልል 47 ሀገራት ውስጥ ከ 10 ያነሱ ሀገራት ናቸው የ 2020 ፖሊዮን የማስወገድ ግብን ለማሳካት መስመር ውስጥ ያሉት ተብሏል፡፡

ግቡ አዲስ በፖሊዮ የሚጠቃ ሰው ከ 1 ሚሊዮን ህዝብ አንድ ወይም ከዚያ በታች እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡

በአፍሪካ ሁኔታው፤ በኮቪድ 19 ምክንያት የባሰ ወደ ኋላ እንዲጎተት አድርጎታል፡፡

ከባለፈው ተመሳሳይ አመት አንፃር በ2020 መጀመርያው ሩብ አመት ያለው መረጃ እንደሚያሳየው 1.5 ሚሊዮን ተጨማሪ አፍሪካዊ ህፃናት የመጀመርያውን ዙር የፖሊዮ ክትባት ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በቀጣዮቹ ወራት ለህፃናቱ ክትባቱ በአፍሪካ በአግባቡ የማይደርስ ከሆነ ፖሊዮ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ስጋት እንዳለ የአለም ጤና ድርጅቱ ጨምሮ ገልጧል፡፡

በ2019 4.5 ሚሊዮን ህፃናት የፖሊዮ ክትባት ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

በአፍሪካ በ2018 በአብዛኛው እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ 52 ሺህ 600 ህፃናት በፖሊዮ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በሔኖክ አስራት
ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *