የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተጨማሪ አራት የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከል ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ።

የኮሮና ቫይረስ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ተጨማሪ የኮቪድ ምርመራ ማዕከላት ለመክፈት ማሰቡን ቢሮው አስታውቋል።

የቢሮው ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዋሌ በላይነህ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የአማራ ክልል በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ከሆኑ ክልሎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁንም በሰምንት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከላት እስከ ትናንት ድረስ 28 ሺህ 621 ናሙናዎች የመረመረ ሲሆን 504 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

በኮሮና ከተጠቁ 504 ሰዎች ወስጥም 398 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገግሙ የአምሰት ሰዎች ህይወት ማለፉን ሃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ የውጭ አገራት የጉዞ ታሪክ እና በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ንኪኪ ያላቸው ሰዎች ቁጥር መጨመር እንዳለ ሆኖ የቫይረሱ ስርጭት በማህበረሰብ ደረጃ እየተስፋፋ በመምጣቱ ተጨማሪ የኮሮና ምርመራ ማዕከላትን ማቋቋም የግድ ማስፈለጉንም አቶ ዋለ ገልጸዋል።

በዚህም በደብረ ማርቆስ፣ደብረታቦር እና መተማ አዲስ የምርመራ ማዕከላትን ለማቋቋም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።

በመቀጠልም በከሚሴ ከተማ አራተኛ የኮቪድ ምርመራ ማዕከል ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ ዋሌ ነግረውናል።

በኢትዮጵያ ዕለታዊ የኮቪድ ናሙና የመመርመር አቅምን በ52 የምርመራ ማዕከላት 13 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ ሲሆን አሁን ላይ ከ10 ሺህ በታች ነው።

በአማራ ክልል ደግሞ በእያንዳንዱ የኮቪድ መመርመሪያ ማዕከላት በየዕለቱ 300 ናሙናዎችን ለመመርመር ቢታቀድም አሁን ላይ ግን ከ100 ናሙናዎች በላይ ማለፍ አለመቻሉን ከክልሉ ጤና ቢሮ ሰምተናል።

በሙሉቀን አሰፋ
ሐምሌ 23 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.