ኢትዮጵያ በኮሮና ተጠቂዎች ከአፍሪካ ሰባተኛ ላይ ስትገኝ ከአለም ደግሞ 68ኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያቶች በኃላ የቫይረሱ ስርጭት እና የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡

እስካሁን ድረስ ሀገሪቷ ከ444 ሺህ በላይ ዜጎችን የመረመረች ሲሆን 19 ሺህ 289 ዜጎች ደግሞ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡

ከነዚህም መካከል 7 ሺህ 900 ያህሉ ያገገሙ ሲሆን 11 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ ከቫይረሱ እንዲያገግሙ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 336 ዜጎች ህይወታቸው ሲያልፍ 153 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ህሙማን ክፍል እንደሚገኙ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

ከአህጉሩ ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት የምትገኝ ሲሆን ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ በቫይረሱ ሲያዙ ከ8 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡

ግብጽ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎች የሚገኙባት ሀገር ስትሆን 94ሺህ ዜጎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡

እንዲሁም 4ሺህ ስምት መቶ ያህል ዜጎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

በዓለማችን ደግሞ የበሽታው ስርጭት መቆጣጠር ተስኗታል የተባለችው አሜሪካ ከ4 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ ሲያዙባት 159 ሺህ ያህል ዜጎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ሀገሪቷ ከአለም በተጠቂዎች ቁጥርም በቀዳሚነት እየመራች ነው የምትገኝው፡፡

ብራዚል ከአለም ተከታዩን ደረጃ ስትይዝ 2.7ሚሊየን የሚጠጋ ህዝቧ በቫይረሱ ሲያዝ ከ94ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡

ባጠቃላይ በአለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ድረስ 18 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ በቫይረሱ ሲያዝ ወደ 698 ሺህ ያህል ዜጎች ህይወታቸው አልፏል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.