የአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ላይ ባደረገው አሰሳ ከሁለት ሽህ በላይ ምልክት ያሳዩ ሰዎች መለየቱን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ እንዳለዉ የኮሮና ስርጭትና ስጋት በክልሉ እየተስፋፋ መምጣቱን ገልጾ፣ኮሮናን ለመከላከል የተቋቋመዉ ግብረ-ሃይልም ህብረተሰቡ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረዉም ሆነ አስፈላጊ ሲሆን ምርመራ እንዲያደርግ በየ ቤቱ እየተንቀሳቀሰ ጥንቃቄ የተሞላበት አሰሳ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በዚህም ለሁለተኛ ዙር በ 3 ሚሊዮን 189 ሽህ 2 ቤቶች ላይ ባደረገዉ አሰሳ 2 ሽህ 18 ሰዎች ኮሮና መሰል ምልክት በማሳየታቸዉ እንዲመረመሩ አድርጎ ቫይረሱ የተገኘባቸዉን ወደ ማገገሚያ ማዕከላት፤ነጻ የሆኑትን ደግሞ ወደ መደበኛ ህይወታቸዉ እንዲመለሱ ማድረጉን አስታዉቋል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዋሌ በላይነህ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት
ቀደም ሲል ምርመራዉ ያተኩር የነበረዉ ቫይረሱ ከተገኘባቸዉ ሰዎች ጋር ግንኙነት አላቸዉ በሚል የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ብቻ እንደነበር ገልጸዉ፤ በአሁኑ ወቅት ግን የምርመራ ማዕከላትን ወደ 8 ከፍ በማድረግና የምርመራ አቅምን በማሳደግ ሳልና ሙቀት ያለባቸዉ ሰዎች ሁሉ እንዲመረመሩ እየተደረገ ነዉ ብለዋል፡፡

በክልሉ የውጭ አገራት የጉዞ ታሪክ እና በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ንኪኪ ያላቸው ሰዎች ቁጥር መጨመር እንዳለ ሆኖ የቫይረሱ ስርጭት በማህበረሰብ ደረጃ እየተስፋፋ በመምጣቱ ተጨማሪ የኮሮና ምርመራ ማዕከላትን ማቋቋም የግድ ማስፈለጉንም አቶ ዋለ ገልጸዋል።

በዚህም በደብረ ማርቆስ፣ደብረታቦር እና መተማ አዲስ የምርመራ ማዕከላትን ለማቋቋም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።

በመቀጠልም በከሚሴ ከተማ አራተኛ የኮቪድ ምርመራ ማዕከል ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ ዋሌ ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶችም ስርጭቱ ከዉጭ በመጡና ከክልሉ ወደ ሌላ ክልልና ከተማ በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ በርከት ብሎ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

ክልሉ በእያንዳንዱ የኮቪድ መመርመሪያ ማዕከላት በየዕለቱ 300 ናሙናዎችን ለመመርመር ቢታቀድም አሁን ላይ ግን ከ100 ናሙናዎች በላይ ማለፍ አለመቻሉን ከክልሉ ጤና ቢሮ ሰምተናል።

በሙሉቀን አሰፋ
ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.