ኢትዮ ሊዝ ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የእርሻ ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ለገበሬዎች አስረከበ።

በኢትዮጵያ በሊዝ ፋይናንስ ዘርፍ በመሰማራት የመጀመርያው የውጭ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ሊዝ የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ 16 ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሮች እና ለማህበራት ማስረከቡን ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎቹን ወደ አገር ውስጥ ያስገባው የኢትዮጵያ መንግስት በግብረናው ዘርፍ ለማዘመን የያዘውን ስትራቴጂ ለመደገፍ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ጋር ያደረገውን ሰምምንት ተከትሎ ነው።

ስምምነቱም እነዚህን ውድ የሆኑ የግብርና ማቀነባበሪያ መሳሪያዎችን መግዛት የማይችሉትን አርሶ አደር ገበሬዎችን በአጭር ጊዜ ባለቤት የሚያደርግ ይሆናል ተብሏል።

በዚህኛው ዙር የተካሄደው ርክክብ እስካሁን ድረስ ያስረከባችውን የግብርና መሳሪያዎች ቁጥር ወደ አንድ መቶ ያደረሰ ሲሆን አጠቃላይ ወጪያቸው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው።

ከነዚህም በተጨማሪ ኩባንያው በመጪው መስከረም እና በጥቅምት ወራት 10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተጨማሪ መሳሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልጉትን ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ በመግለጫው ጠቁሟል።

የኢትዮ ሊዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ግሩም ፀጋዬ በርክክቡ ውቅት በበኩላቸው “ በተከታታይ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባናቸው ያሉት የግብርና መሳሪያዎች ኩባንያችን የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ የማዘመን እቅድ ለማሳካት የበኩሉን እየሰራ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን ከዚህም እንቅፋት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጦት መፍታት ችለናል” ብለዋል።

አቶ ግሩም አክለውም “ ዘላቂነት ያልው የግብርና ማዘመን ስራ የአርሶ አደሩን አቅም በመገንባት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወትና ምርታማነትን እና ገቢን ሊያሻሽል እንዲሁም የምግብ ዋስትናን እና አኗኗር ያሻሽላል፡፡” ብለዋል።

የኢትዮ ሊዝ አርሶ አደሮች ከመደገፍ በተጨማሪ ለኦፕሬተሮች ፣ ለረዳቶች ኦፕሬተሮች እና ለተለያዮ ባለሙያዎች ፣ የስራ ዕድልን የሚፈጥር እንደሆነ በሻሽመኔ ከተማ በተደረገው ርክክብ ላይ ተነግሯል ፡፡

አትዮ ሊዝ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ በተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ በ400 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተ ኩባንያ ነው፡፡

ኩባንያው ለእርሻ፣ ለሕክምናና አምራች ኢንዱስትሪ የሚውሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች በኪራይ ለማቅረብ የሚያስችለውን የሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ሊዝ የካፒታል እቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ በመለየት እና በመግዛት፤ አስፈላጊ ጥገናዎችን እና አግባብነት ባለው ሁኔታ አገልግሎት ላይ መዋላቸውን የመቆጣጠር ሃላፊነት ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም ተከራዩ ወይንም አገልግሎቱን ያገኘው አካል መሳሪያዎችን መግዛት የሚችልበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡

ኢትዮ ሊዝ ወደስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፣ ለግብርና፤ ለጤና፤ ለኢነርጂ፤ ለምግብ ማቀነባበር አገልግሎት ሰጪዎች የካፒታል እቃዎችን አቅርቧል፡፡

ድርጅቱ እስካሁን ከ60 በላይ ከሚሆኑ ደንበኞች ጋር የካፒታል እቃዎች አቅርቦት ስምምነትም አድርጓል፡፡

ኢትዮ ሊዝ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ኩባንያ ሲሆን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ እአአ በ2017 የአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ኩባንያ አካል በመሆን ስራው የጀመረ ተቋም ነው፡፡

ኩባንያው በአፍሪካ የሊዝ አገልግሎት ያተዳረሰባቸውን ገበያዎች ለማገልገልና አቅምን ያገናዘበ ብድር ለማቅረብ የሚሰራ ተቋምም ነው፡፡

በዳንኤል መላኩ
ሐምል 30 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *