መንግስት በአስቸኳይ አዋጁ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ የኢትዮጲያ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ጠየቀ።

ህብረቱ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳለው አዋጁ አብዛኛውን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚገድብ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ አዋጁ የወጣ ሰሞን አፈፃፀሙ ላይ ክፍተቶች ነበሩ በነዚህም ክፍተቶች ምክንያት አላስፈላጊ እስር እና ሞት በዜጎች ላይ ይደርስ ነበር ብሏል፡፡

የህብረቱ ዳይሬክተር እና የህግ ባለሙያ አቶ መሱድ ገበየሁ እንዳሉት አዋጁ የወጣ ሰሞን የግል አሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው እገዳ፣ ሰዎች ለቫይረሱ በሚያጋልጥ ሁኔታ ለበዓል ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲጓዙ ቶሎ እርምጃ አለመወሰዱ፣ ማስክ አላደረጋችሁም በሚል በወንጀል ተከሰው ብዙ ሰዎች ጥፋተኛ መባላቸው እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋችኋል በሚል ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ለቫይረሱ በሚያጋልጥ መልኩ በርካታ ሰዎች መታሰራቸው በአዋጁ አፈፃፀም ላይ የታዩ ክፍተቶች ናቸው ብለዋል፡፡

አዋጁ የወጣው የህረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ እና የሰዎችን በህይወት የመኖር መብትን መጠበቅ ሆኖ ሳለ ከአዋጁ ዓላማ ጋር የማይገናኙ አፈፃፀሞች ሲከናወኑ ነበርም ብለዋል፡፡

ይህ አዋጅ ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነም ተሳፋሪዎች እጥፍ የሚከፍሉበት መመሪያ ላይ ፣የግል ድርጅቶች ሰራተኛን ማባረር አይችሉም በሚለው መመሪያ ላይ እንዲሁም የፊት ጭምብል አላደረክም ብሎ ማሰር ግለሰቡን ከማስተማር አንፃር ያለው ፋይዳ አነስተኛ በመሆኑ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል ብለውናል አቶ መሱድ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም የወጡ መመሪያዎችን በተላለፉ ሰዎች ላይ በወንጀል የሚጠየቁበት ሂደት ከወንጀል ህግ መርህ ጋር የሚጻረሩ ናቸው፤ ጥሰቶቹ የወንጀል ባህሪ ሳይሆን የአስተዳደር ባህሪ ያላቸው በመሆኑ ይህም ሊሻሻል ይገባል ይላሉ የህብረቱ ዳይሬክተር፡፡

በተለይ ባለፉት ጊዚያት በሀገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በአዲስ አበባ ዙሪያና በኦሮሚያ ክልል ከተሞች በርካታ ሰዎች የታሰሩበት ሲሆን በአዋጁ ምክንያት ከቤተሰቦቻችን ጋር መገናኘት አልቻልንም የሚሉ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ለፍርድ ቤት ይቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወረርሽኙን ለመከላከል የእስረኞች ጥየቃ ላይ ክልከላ ቢያደርግም ምግብ እንዲገባና ቤተሰብ እየሄደ በቀን አንድ አንድ ሰው እንዲጠይቅ ማረሚያ ቤቶች እያመቻቹ እንደሆነ ታዝቢለሁና ቫይረሱን ከመከላከል አንፃር እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ ድርጅቱ አሳስቧል፡፡

ይህንና መንግስት የዜጎችን ህይወት ለመጠበቅ በሚል የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማሻሻያ አድርጎ ቢያራዝመው ተቃውሞ እንደሌለውምም ህብረቱ አስታውቋል።

በትግስት ዘላለም
ነሀሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *