በኢትዮጵያ ከኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ (ICL) ውጪ ለሌሎች የግል ሆስፒታሎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የማድረግ ፈቃድ አለመስጠቱን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በአዲስ አበባ በህብረተሰቡ ዘንድ ወደ ተለያዩ የግል የጤና ተቋማት የመሄድና የኮሮና ቫይረስ ምርመራን የማድረግ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ታዝበናል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም ይህንን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩትን ስለጉዳዩ ጠይቀናል።

ኢንስቲትዩቱ እንዳለውም የግል የጤና ተቋማቱ የኮሮና ቫይረስ ናሙማን መውስድ እንጂ የኮሮና ቫይረስ ምርመራን አለመጀመራቸውን ገልጿል።

በህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የCOVID 19 ምክትል አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ምርመራን ለመጀመር አምስት ላብራቶሪዎች ውድድር አድርገው ነበር።

ለምርመራው ተገቢውን መስፈርት አሟልቶ በመገኘቱ በአሁኑ ሰዓት ከግል የጤና ተቋማት መካከል የኮሮና ቫይረስ ምርመራን እያካሄደ ያለው ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ (ICL) ብቻ መሆኑን አቶ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በሃገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ የግል ጤና ተቋማት የኮሮና ቫይረስ ምርመራን ማድረግ ሳይሆን ናሙና በመውሰድ በመንግስት እውቅና ወዳላቸው ላብራቶሪዎች ናሙናዎችን የመላክ ሂደትን በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ማወቅ እንደሚገባው አስታውቀዋል፡፡

ይህ የግል ተቋምም ወደ ውጪ ጉዞ ለሚያደርጉ መንገደኞች ብቻ ምርመራውን እንዲያደርግ ፍቃድ ማግኘቱን ነው አቶ ዘውዱ የነገሩን፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ እየተደረገ ካለው የምርመራ ሂደት ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ያለው አንድ ግለሰብ በተቻለ መጠን እራሱን መለየትና ከእንቅስቃሴ መገደብ እንደሚኖርበት እንዲሁም ለበለጠ መረጃ በ 8335 ወይንም በ 952 መደወል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

አንድ ግለሰብ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ሲኖረውና ተጓዳኝ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች ይህ ሁኔታ ካጋጠማቸው ያለምንም ወጪ የመንግስት የላብራቶሪ ተቋማት ናሙናውን ባሉበት ቦታ ሆነው ሊወስዱ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩንም ነግረውናል፡፡

በየውልሰው ገዝሙ
ነሀሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *