የአሜሪካ የጤና ባለሙያዎች ሩሲያ አገኘሁ ባለችው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ላይ ዕምነት እንደሌላቸው ተናገሩ።

የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት ረፋድ ለአርቲ የዜና ወኪል ሩሲያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማግኘቷን መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንን ክትባትም የሩሲያ ፕሬዘዳንት ፑቲን ሴት ልጅ መከተቧ እና ፈዋሽነቱ መረጋገጡ መገለጹም አይዘነጋም።

በሞስኮ ጋማሊያ ኢንስቲትዩት ተፈበረከ የተባለው ይህ ክትባት ከሩሲያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅና ማግኘቱ ተገልጾ ነበር፡፡

ሩሲያ የኮቪድ-19 ክትባት በብዛት ማምረት እንደምትጀምር በገለጸች ማግስት በርካታ የአሜሪካ የጤና አመራሮች እና የክትባት ባለሙያዎች ግን ክትባቱ አስተማማኝ እና ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ደረስ ክትባቱ በሰዎች ላይ ስለተደረገው ሙከራ አልተለቀቀም እናም የምዕራፍ ሶስት ሙከራን አላለፈም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የፊሊፒንሱ ፕሬዝደንት ሮድሪጎ ዶተርቲ የሩሲያን የኮሮና መድሃኒት ለመሞከር ፍቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የፊሊፒንስ ፕሬዝደንት ሮድሪጎ ዱተርቲ በሩሲያ ኮሮና ቫይረስ ክትባት ላይ እምነት እንዳላቸውና ለሙከራው በጎ ፈቃደኞች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝደነት ዱተርቲ እንደሚሉት ሩሲያ የሞከረችው ክትባት ለሰው ልጆች በጣም ጥሩ እንደሆነ አምናለሁ፣እስከ ታህሳስ ወር ድረስም ከኮሮና ቫይረስ ነጻ እንሆናለን ሲሉ በተስፋ መናገራቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ነሀሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.