በአዲስ አበባ ኮሮናን ለመከላከል በሚል እጥፍ የተደረገው የትራንስፖርት ታሪፍ ባለበት ይቀጥላል ተባለ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የመጫን አቅማቸው በ50 ከመቶ እንዲቀነሱ በአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮም በከተማው የትንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡትንም የመጫን መጠናቸው በ50 ከመቶ እንዲቀንሱ እና ክፍያው እጥፍ እንዲሆን ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

መመርያው አሁንም ለተወሰኑ ጊዜያቶች እንደሚቀጥል ነው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያስታወቀው፡፡

እንደዚሁም በመመርያው መሰረት የተቀመጡትን ሁሉም የቅጣት ህጎች ተግባራዊ ሆነው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡

ይህንንም መመርያ ባለፉት ወራት ከተማ አስተዳደሩ እና ትራንስፖርት ቢሮው ተግባራዊ አድርጎ ክትትል እና ቁጥጥር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በከተማው የትራንስፖርት ሰልፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ቢሮው አሽከርካሪዎች በወንበር ልክ እንዲጭኑ እና ታሪፉም ወደ ነበረው ለመመለስ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በከተማው አሁን የሚስተዋለው የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍም ትራንስፖርት ቢሮው 150 ሀገር አቋራጭ አውቶቢሶችን በከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እንደቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ አረጋዊ ነግረውናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 50 የሚጠጉ የአስጎቢኚ ተሽከርካሪዎችንም ለትራንስፖርት አገልግሎት ለማዋልም ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሀሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.