የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዳለዉ የተለያዩ ድርጅቶች ስራ ተቀዛቅዟል፤የመክፈል አቅምም የለንም በሚል ስራተኞችን መቀነሳቸዉን ገልጿል፡፡
የቢሮዉ ምክትል ሃላፊ አቶ ተክሌ ደሬሳ እንደሚሉት አሰሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰራተኛን ማባረር እንደማይፈቅድ ጥንቅቅ አድርገዉ እያወቁም አዋጁን በመጣስ ሰራተኛን ያባረሩ ድርጅቶች መኖራቸዉን ታዝበናል ብለዋል፡፡
እስካሁንም በከተማዋ ብቻ ከ16 ሽህ በላይ ሰራተኞች ከስራ ተባረናል ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸዉን ነግረዉናል፡፡
ከስራቸው ተሰናብተው ወደ ቢሮው ለአቤቱታ ያልመጡ ተሰናባች ሰራተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይበቃል።
አሰሪዎች ሰራተኞቻቸዉን እንዲቀነሱ በማባበል እንዲለቁ ማድረግ ፣ወደ ኮንትራት በማዘዋወር ለማባረር በማመቻቸትና ብሎም አስገድዶ ስራ እንዲለቁ በማድረግ ስራቸዉን ስለማጣታቸዉ ስራተኞች መናገራቸዉን ገልጸዋል፡፡
ባደረግነዉ ማጣራትም 55 ድርጅቶች በቀጥታ ሰራተኞቻቸዉን ማገዳቸዉንና 150 የሚሆኑት ደግሞ ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል በሚል ለመክፈል ፈቃደኛ አንዳልሆኑ ነዉ የተናገሩት፡፡
ሆቴሎች፣ ካፌዎች ና ሬስቶራንቶች ደግሞ በዋናነት ሰራተኛን በማሰናበት ቀዳሚ ተቋማት መሆናቸውንም አቶ ተክሎ ገልጸዋል።
በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ግን ሰራተኞቻቸውን አለማሰናበታቸው ተገልጿል።
በዋናነት ለሰራተኞች ጥቅም የቆምን ብንሆንም ለኛ ሰራተኞችም ሆኑ አሰሪዎች ያስፈልጉናል የሚሉት ምክትል ሃላፊዉ፣ ችግሮችን በመወያየት ለመፍታት በተደረገ ጥረት ከቀረቡ ቅረታዎች 80 በመቶ የሚሆኑትን መፍታት ተችሏል ብለዋል፡፡
ከእኛ አቅም ዉጭ የሆኑ 150 በላይ ድርጅቶችን ደግሞ ህጋዊ መፍትሔ እንዲያገኙ ወደ አስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።
ምክትል ሃላፊዉ፣ይህን አስቸጋሪ ወቅት በመደጋገፍ ማለፍ እንደሚገባ ጠቅሰዉ፣ ድርጅቶች ሰራተኛን ከማባረር ይልቅ መንግስትን በመጠየቅ የብድርና ሌሎች ድጋፎችን የሚያገኙበትን መንገድ ቢያመቻቹ የተሸለ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በሙሉቀን አሰፋ
ነሀሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም











