በመተከል ዞን የህዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ የታጠቁ ሃይሎች መደምሰሳቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ።

በዞኑ ከ20 ቀናት በፊት ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል እና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥርም 225 መድረሱ ተገልጿል።

የክልሉ መንግስት ኮሚንኬሽን ዳሬክተር አቶ መለሰ በየነ ለኢት ኤፍ ኤም እንዳሉት በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ ፒሬ አካባቢ 5 ታጣቂዎች ሲገደሉ 3 ተጨማሪ ግለሰቦች እስከ ትጥቃቸው በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች መማረካቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ሀይሎች በመተከል ዞን በጉባ እና ወንበራ ወረዳዎች የሚኖሩ ነባር የጉምዝ የሀገር ሽማግሌዎችን ለብልፅግና ፓርቲ መረጃ እየሰጣችሁ ነው በሚል በማገትና ጫካ ውስጥ በመውሰድ ድብደባ በማድረስ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የመፈፀም ድርጊቶችን ሲፈፅሙ እንደነበረ ገልፀዋል፡፡

የክልሉ መንግስት እነዚህ መረጃዎች እንደደረሱን ከመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ሀይል ጋር በመቀናጀት በቀጥታ ከእነዚህን ሀይሎች ጋር ውጊያ መጀመሩን ተናግረዋል።

ታትጥቀው በጫካ ከሸፈቱት ሀይሎች ጋር በነበረው የተክስ ልውውጥ ብዙዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል በመጀመሩ ተስፋ እየቆረጡ በተበታተነ ሁኔታ እየተማረኩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በወንበራ ወረዳ ፒሬ በሚባል አካባቢ መከላከያ ሰራዊት በወሰደው ኦፕሬሽን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት በተደረገው የተክስ ልውውጥ 5 ታጣቂዎች በኦፕሬሽኑ መገደላቸውን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም 3 ተጨማሪ ግለሰቦችን እስከትጥቃቸው በፀጥታ አካሉ እንደተማረኩ አክለው ገልፀዋል፡፡

የተቀሩትን ሀይሎች በፍጥነት ለመቆጣጠር ጥረት ቢደረግም ያመለጡ አሉ ያሉት አቶ መለስ እነርሱን አድኖ በቁጥጥር ስር ለማዋል እርምጃዎች እንደቀጠሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ጫካ ሸፍተው የነበሩት እነዚህ ታጣቂዎች በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ጉባና ወንበራ በሚባሉ ወረዳዎች በውስጥም በውጭም የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ ተናግረዋል።

እነዚህ የታጠቁ ሀይሎች ከመከላከያ ሰራዊት በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆኑ መረጋገጡንም ሃላፊው ነግረውናል።

አቶ መለሰ አክለውም የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታዎችን ለማስተጓጎል ከህወሀትና ከግብፅ ተልዕኮ የተሰጣቸው መሆኑን ደርሰንበታል ይላሉ፡፡

አሁን የሸፈቱት ታጣቂዎች ተስፋ እየቆረጡ እና ቁጥራቸውም እየመነመነ መሆኑን የሚናገሩት አቶ መለስ እስካሁንም በክልሉ ሁከት ሲያስነሱ የነበሩ የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ225 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል ብለዋል፡፡

የክልሉና የፌደራል መንግስት ለስፍራው ልዩ ትኩረት በመስጠት የአካባቢው ፀጥታ እንዳይደፈርስ በቁርጠኝነት ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በዚህም አርኪ ውጤቶች ታይተዋል ያሉት ሀላፊው አሁን ላይ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በደረሰ አማረ
ነሀሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *