የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ በማስመሰል ተመሳሳይ ወንጀል የሚፈፅሙ መኖራቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የግል ተበዳይ ወይዘሮ ራውዳ መሃመድ ነሃሴ 2 ቀን 2012 ዓ/ም ከቀኑ 6 ሰዓት በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1-19439 አ/አ በሆነ ሚኒባስ ታክሲ ከካርል አደባባይ ወደ ዘነበወርቅ ትርፍ ተጭና በመጓዝ ላይ እንዳለች አሽከርካሪው”ጎንበስ በይ ትራፊክ ፖሊስ እንዳያይሽ ሰላት ረዳቱም ትራፊክ ፖሊሶች በሞተር ብስክሌት እየተከተሉን ነው” በማለት እንዳዋከቧት አጠገቧ የነበረው ተሳፋሪ በእጇ የያዘችውን ተንጠልጣይ ቦርሳ አምጪው ልያዝልሽ ብሎ እንደተቀበላት ገልፃለች፡፡
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ደሳለኝ ስጋቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ስትደርስ “ውረጂና በሌላ ታክሲ ነይ “ብለው ሲያስወርዷት ቦርሳዋ ውስጥ የነበረው 4ሺ 500 ብር መሰረ ቁን በማወቋ ሰዎች እንዲረዷት ያሰማቸውን የድረሱልኝ ጩኸት የሰሙ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች እና የፖሊስ አባላት ደርሰው ሾፌሩን ከሌላ አንድ ተጠርጣሪ ጋር እንደያዙላት ወይዘሮ ራውዳ ተናግራለች፡፡
ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ብሩን ይዘው መሰወራቸውን በመካኒሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ምክትል ሳጅን ምንይበል ውድዬ ተናግረው በተያዙት ጓደኞቻቸው አማካይነት ተደውሎላቸው ገንዘቡን እንዲመልሱ ሲጠየቁ በአካል አንመጣም ብለው የግል ተበዳይን የባንክ የሂሳብ ቁጥር ጠይቀው ገንዘቧን በባንክ ገቢ አድርገውላታል ብለዋል፡፡
በተያዙት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ መቀጠሉን እና ያልተያዙትንም ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መርማሪው አስረድተዋል፡፡
የግል ተበዳይ ወይዘሮ ራውዳ መሃመድ በበኩሏ ገንዘቡ ወንጀሉ ከተፈፀመ ከደቂቃዎች በኋላ ገቢ እንደተደረገላት አረጋግጣለች፡፡
በተመሳሳይ ዜና በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-57733 ኦ.ሮ ዶልፊን የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 3 ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል፡፡
የጣቢያው ወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን ነዋይ ሰለሞን እንዳስረዱት ተጠርጣሪዎቹ ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ/ም ከቀኑ 6 ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ በመምሰል ሰይፉ ላለሞ የተባለውን የግልተበዳይ ከጀርመን አደባባይ ወደ አየር ጤና ከጫኑት በኋላ “አጠገብህ ያለውን እስፒከር አስተካክለው” ብለው በማዘናጋት 3ሺ 500 ብር ግምት ያለው ሞባይል ስልክ ከኪሱ ወስደው እና ምክንያት ፈጥረው በማስወረድ ሊሰወሩ ሲሞክሩ የግል ተበዳይ ስልኩ መወሰዱን ስላወቀ ወዲያውኑ በትራፊክ ፖሊሶች እጅ ከፍንጅ እንዲያዙ አድርጓል፡፡
ወንጀል መርማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ በመምሰል እና ሴቶችን ያካተተ ቡድን በማደራጀት በተለያዩ የማዘናጊያ ስልቶች የሿሿ ወንጀል የሚፈፀሙ መኖራቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ቢቻል የተሳፈረበትን ተሸከርካሪ ሰሌዳ የመመዝገብና ከመውረዱ በፊት ኪሱን እና ሌሎች ንብረቶቹን የማረጋገጥ ልምድ ቢያዳብር ወንጀሉን መከላከል እንደሚቻል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ነሀሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም











