የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማሊ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት አወገዘ።

ተመድ የማሊውን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቦውካር ኬዬታ ከስልጣን እንዲለቁ ያስገደዳቸውን መፈንቅለ መንግስት አውግዟል፡፡

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሁሉም የመንግስት ባለስልጣናት ከእስር በአስቸኳይ እንዲለቀቁና ህገ መንግስታዊ ስርአቱ እንዲመለስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ወታደሮቹ ይሄን እያደረግን ያለነው ሀገሪቱ ወደ ተጨማሪ ትርምስ እንዳታመራ ነው ብለዋል፡፡

ህዝባዊ መንግስት እናቋቁማለን፣አዲስ ምርጫ እንዲከናወንም እንደርጋለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

እስከ ሰሀራ በረሀ የምትለጠጠው ሰፊዋና ከአለም ደሀ ሀገራት መካከል አንዷ ማሊ በመንግስታዊ ስርአቷ ላይ በርካታ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶችን አስተናግዳለች፡፡

በአሁን ሰአት ደግሞ የአክራሪ ጂሀዲስቶችን ጥቃት ለመቆጣጠር እየታገለችና በብሄር ግጭት እየታመሰች ትገኛለች፡፡

ኪዬታ በ 2018 ለ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ያሸነፉ ሲሆን ከሰኔ ጀምሮ ግን ከፍተኛ የአደባባይ ላይ ተቃውሞ እየገጠማቸው ነው፡፡ በሙስና፣ በተጎዳው ኢኮኖሚ፣ ግጭት በፈጠረው የህግ አውጪ ምርጫ የተቆጡ ሰልፈኞች ቁጣቸውን እየገለፁ ከርመዋል፡፡

በወታደሮቹም በኩል በክፍያና ከአክራሪ ጂሃዲስቶች ጋር ከሚፈጠር ግጭት ጋር በተያያዘ ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች ያለፉ ታሪኮች ናቸው ፤ በዚህ ዘመን ልንቀበላቸው አንችልም ሲል ማሊን አግዷታል፡፡

የሆነ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር ወታደሮች የህዝቡን ፍቃድ ነው እየፈፀምን ያለነው በማለት መፈንቅለ መንግስት መፈፀም በምንም አይነት መስፈርት ተቀባይነት የለውም ብሏል ህብረቱ፡፡

የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ህብረት (Ecowas) አባል ሀገራትም ማሊ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እየወሰዱ ነው፡፡ ከውሳኔ ሰጪነት ከማስወገድ ድንበር እስከመዝጋት እንዲሁም ወደ ማሊ የሚደረጉ የገንዘብ ፍሰቶችን እስከማገድ የደረሱ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር ማይክ ፖምፒዮ በትዊተር ገፃቸው መፍንቅለ መንግስቱን በጥብቅ ያወገዙ ሲሆን የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ከአሸባሪዎች ጋር የሚደረገው ትግል እና ዲሞክራሲና የህግ የበላይነትን መጠበቅ የማይለያዩ ናቸው በማለት ህዝባዊ ምንግስቱ በአስቸኳይ ወደ ቦታው እንዲመለስ አሳስበዋል፡፡

በሔኖክ አስራት
ነሀሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.