የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ልዩነቱን ለመፍታት በዝግ እየመከረ መሆኑን አስታወቀ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ በፖርቲው ውስጥ የተከሰተውን ልዩነት ለመፍታት ውይይት መቀመጡን ተናግሯል፡፡

የፓርቲው ቃላ አቀባይ የሆኑት አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለኤትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በፓርቲው ውስጥ የተከሰተውን ልዩነት ለመፍታት ውይይት ላይ እንገኛለን ይሁን እንጂ ዝርዝር ጉዳዩን መናገር አልችልም ብለዋል፡፡

በዚህ የዝግ ውይይት ላይ አደራዳሪዎች በመሳተፍ ላይ እንዳሉ ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለረዥም ጊዜ የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉትን አቶ ዳውድ ኢብሳን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጋር በትብብር ለመሥራት ፈቃደኛ አይደሉም በማለት እግድ ጥሎባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው ምክትል የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበሩን አቶ አራርሶ ቢቂላ፣ የሥራ አስፈጻሚው አባሉን አቶ ቶሌራ አዳባንና አቶ ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ ስድስት አመራሮችን ከፓርቲው አግደው ነበር፡፡

ፓርቲው ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ክፍፍልና የአመራሮች መተጋገድ የመጣው ከሳምንታት በፊት የኦነግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበሩን ያላሳተፈ ስብሰባ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

በወቅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለአቶ ዳውድ አስቀድሞ አሳውቆ እሳቸውም ስብሰባው እንዲካሔድ የተስማሙ ቢሆንም፣ በኋላ የስብሰባው ዋዜማ ምሽት ላይ አቶ ዳውድ ስብሰባውን ሕገወጥ እንዳሉትና ስብሰባው እንደሚካሔድም እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

አሁን እንዲህ አይነቱን ልዩነትና ክፍፍል ለመፍታት ይረዳል የተባለ ስብሰባ ነው እያደረግን ያለነው ይላሉ አቶ ቀጀላ፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ነሀሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.