ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን ለውድቀት እንደዳረጓት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ተናገሩ።

የቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ ጆን ባይደን የቀድሞ አለቃ ባራክ ኦባማ በቀጥታ ስርጭት በሰጡት አስተያየት ዶናልድ ትራምፕን ራሳቸው ወድቀው ሀገሪቷን በውድቀት ጎዳና እየመሯት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኔ ተከታይ የኔን ራዕይ የራሱ እንዲያደርግ፣ የኔን ፖሊሲ እንዲያስቀጥል አልጠብቅም ያሉት ኦባማ ለሀገራችን ሲባል ግን ዶናልድ ትራምፕ ስራቸውን በቁም ነገር እንደሚይዙት ተስፋ አድርጌ ነበር፤ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው ብለዋል፡፡

አራት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ትራምፕ ራሳቸውንና ጓደኞቻቸውን ከመርዳት በዘለለ የተቀመጡበትን ስልጣን በመጠቀም ሀገራችንንም ማንንም ለመርዳት ፍላጎት አሳይተው አያውቁም ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡

የፕሬዝዳንትነቱንና የቦታውን ትርጉም በቅጡ ያልተረዱት ትራምፕ ሁሌም የሚማስኑለትን ትኩረት ለማግኘት ከመልፋት በዘለለ ምንም የረባ ስራ ሳይሰሩ የመጀመርያ የምርጫ ዘመናቸው ሊያልቅ ነው፡፡

የተቀመጡበትን ቦታ እንደ አንድ ተጨማሪ እውነተኛ ታሪክ ላይ እንደሚያጠነጥን የሚዲያ ፕሮግራም ነው የሚመለከቱት ሲሉ ዘልፈዋቸዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በተለመደው በትዊተር ገጻቸው ለኦባማ ዘለፋ ምላሽ ሰጥተዋል።

በኦባማ ንግገር የተከፉ የሚመስሉት ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዲሞክራቶች የምርጫ ዘመቻዬ ላይ ስለላ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

እንዲህ አይነት የስለላ ተግባራት የሀገር ክህደት ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዘመቻዬ ላይ ተፈጸመብኝ ላሉት ስለላ ግን ማስረጃ እንዳላቸው ከመናገር መቆጠባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በሔኖክ አስራት
ነሀሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *