ባለፉት16 ቀናት ብቻ ከ129 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች፣ የታክስ ማጭበርበሮችና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንደተደረሰባቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከሐምሌ 27 እስከ ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት 16 ቀናት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ከ129 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የታክስ ማጨበርበሮች ተደርሶባቸው ለመንግስት ገቢ ተደርገዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ በወቅታዊ ምንዛሪ ተመን 17.8 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 449,700 የአሜሪካ ዶላር፣ በሁመራ መስመር 46 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው 23,000 ግራም ወርቅ በቦሌ ኤርፖርት በኩል ከሀገር ለማስወጣት በቁጥጥር ስር የዋለ ነው፡፡
ሌሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉት ዕቃዎች መካከል የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ አልባሳት፣ ሞተር ሳይክሎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጌጣጌጦች፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ በቱሪስት ስም እና በህገ-ወጥ መንገድ የገቡ ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ዕቃዎች የጉምሩክ ህግን በመተላለፍ ሲዘዋወሩ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተያዙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ሊጭበረበር የነበረ ታክስ በክትትል በመያዝ ገቢ ተደርጓል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ግምታዊ ዋጋ ውስጥ ያልተካተቱ ክላሽንኮቭ፤ የክላሽንኮቭ ካዝና፣ የክላሽ ጥይቶች፣ ሽጉጦች፣ የሽጉጥና የብሬን ጥይቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ዕቃዎቹ በሀረር፣ ሞጆ፣ ባህርዳር፣ ሞያሌ፣ ድሬዳዋ፣ ቡሌ ሆራ፣ኮምቦልቻ ፣ቦሌ ኤርፖርት፣ ጭናክሰን ቅ/ፅ/ቤቶች እና መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ወደ ሀገር ለማስገባትና ከሀገር ለማስወጣት ሙከራ ሲደረግ የተያዙ ናቸው ተብሏል፡፡
ሔኖክ አሥራት
ነሀሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም











