የኖርዌይ የስደተኞች መማክርት በአዲስ አበባ ለችግረኛ ዜጎች ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

የኖርዌይ የስደተኞች መማክርት(NRA) ከአዲስ አበባ ሰራተኛና መህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 ቀውስ በኢትዮጵያ እያስከተለ የሚገኘውን ችግር ለመቀነስ ከ100 በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል።

በዛሬው እለት ድጋፍ የተደረገላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ከቦሌ ፤ ከየካ ፤ ንፋስ ስልክና ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የተለዩ መሆናቸው ተገልጿል።

የኖርዌይ የስደተኞች መማክርት(NRA) ተወካይ የሆኑት አቶ ታደሰ አበበ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ተቋሙ 50 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን እና ከሌላ ሀገራት ለሚመጡ ስደተኞች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።

በኮቪድ-19 ለተጎዱ ኢትዮጵያውያንና ስደተኛ ወገኖች ለያንዳንዳቸው 2 ሺህ 500 ብር የሚገመት የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።

በጠቅላላው ወደ 1.2 ሚሊየን ብር ከ አራት ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ መደረጉን ነግረውናል።

የድጋፍ አሰጣጥ ዝግጅቱ በኮቪድ-19 ለተጎዱ ወገኖች የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የዛሬው መረሀ-ግብር ሁለተኛ ዙር መሆኑን የነገሩን አቶ ታደሰ ከዚህ በፊት ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ለእያንዳንዳቸው 3 ሺህ 500 ብር ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።

ገንዘቡ ከኖርዌይ ፤ ሲውዘርላንድና ኔዘርላንድ መንግስታት የተገኘ ሲሆን በአጠቃላይ ከ5 ሚሊየን በላይ ብር ለኮቪድ-19 ምላሽ ፈሰስ ተደርጓል ብለዋል።

በደረሰ አማረ
ነሀሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.