69 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል እንደሚፈልጉ አንድ ጥናት አመለከተ።

አፍሮ ባሮ ሜትር የተሰኘው ትኩረቱን በህግ እና ፌደራሊዝም ጉዳዮች ያደረገው የጥናት እና ምርምር ተቋም ከፍሪደም ሀውስ ጋር በትብብር ያጠናውን ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።

ጥናቱን የመንግስት ተወካዮች፣መገናኛ ብዙሃን ፣የህግ እና የፌደራሊዝም ምሁራን በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።

ጥናቱ የሕገ መንግስት መሻሻል ጉዳይ፣የፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋዎች ብዛት፣አንቀጽ 39 ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የስልጣን ዘመን፣ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ እና ሌሎች ጉዳዮች በጥናቱ ለተሳተፉ ዜጎች የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው።

በዚህ ጥናት ላይ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ 2 ሺህ 400 ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉ ሲሆን ጥናቱ እና ቀለመጠይቁ ከ6 ወር በፊት መካሄዱም ተገልጿል።

የጥናቱ አቅራቢ እና በኢትዮጵያ የአፍሮ ባሮ ሜትር ናሽናል ፓርትነር አቶ ሙሉ ተካ
እንዳሉት በጥናቱ ከተሳተፉ 10 ኢትዮጵያዊን ሰባቱ ማለትም 69 በመቶ የሚሆኑት ህገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ይፈልጋሉ ብለዋል።

11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ይህ ሕገ መንግስት ከነአካቴው መወገድ አለበት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

18 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ህገ መንግሥቱ ባለበት መቀጠል አለበት ማለታቸው ተገልጿል።

በፌዴራል መንግስት አሁን ካለው የስራ ቋንቋ ተጨማሪ የፌደራል የስራ ቋንቋ መካተት አለበት ያሉት 73 በመቶ ናቸው ተብሏል።

በጥናቱ ከተሳተፉ 37 በመቶዎቹ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው መሃል ላይ ያለው አርማ እንዲነሳ ሲፈልጉ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው አሁን ባለበት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ተብሏል።

ሌላኛው በጥናቱ ለተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ጊዜ ነበር።

በዚህም መሰረት 73 በመቶዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሁለት ምርጫ ጊዜ ብቻ እንዲያገለግሉ ይፈልጋሉ ተብሏል።

የናሙናው መጠን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰራ ወካይነት ያለው ሲሆን ፣ የስህተት ህዳጉ +/- 2 በመቶኛ ና አስተማማኝነት ደረጃው 95 በመቶ መሆኑ የአፍሮ ባሮ ሜትር ጥናት ቡድን አታውቋል።

ኢትዮጵያዊያን በፌዴራሊዝም ስምምነት ቢኖራቸው ብሄርን መሰረት ያደረገ ወይስ መልካ ምድርን አቀማመጥ የሚለው ልዩነት ጥናት ተደርጓል።

61 በመቶ በሀገሪቱ ከአህዳዊነት ይልቅ ፊዴራሊዝም መንግስት እንዲኖር የመረጡ ሲሆን በጥናቱ ከተሳተፉ 37 በመቶዎቹ ደግሞ ፌዴራሊዝም ከፍፋፋ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተገልጿል።

እንዲሁም 49 በመቶ ብሄርን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ያስፈልጋል ሲሉ 48 በመቶዎቹ ደግሞ የክልሎች አወቃቀር መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በዳንኤል መላኩ
ነሀሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *