ኢራን አሜሪካ የ2015ቱን የኑክሌር ስምምነትን ካከበረች ወደ ድርድር ለመመለስ ፈቃደኛ እንደሆነች አስታወቀች።

በወቅቱ የእሜሪካ ፕሬዘዳንት ኦባማ የስልጣን ዘመን ኢራን ከአውሮፓ ሀያላን አገራት ጋር ኑክሌርን ለሰላም እንድታብላላ ተስማምታ ነበር።

ይህ ታሪካዊ የተባለ የኑክሌር ስምምነት በውዝግብ ለተሞላችው ኢራን አዲስ ክስተት ቢሆንም የመካከለኛው ምስራቅን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ለሚፈልጉት ሳውዲ አረቢያ እና ወዳጆቿ አስደንጋጭ ነበር።

ስምምነቱ በተለይም እስራኤልን ክፉኛ ያበሳጨ ነበር።

ኢራን በዚህ ስምምነት ታግዛ የአካባቢውን ሰላም ታውካለች፣ ሽብርተኞችንም ትረዳለች እና መሰል ችግሮችን ትፈጥራለች የምትለው እስራኤል አሜሪካ እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ስምምነቱን ውድቅ እንዲያደርጉ ስትወተውት ቆይታለች።

ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ አዲሱ ፕሬዘዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ግን ስምምነቱ ችግር ገጥሞት ቆይቷል።

ነጋዴው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ የኑክሌር ስምምነት ሳቢያ የአሜሪካን ሰራሽ የጦር መሳሪያዎችን በገፍ የሚሸምቱት ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ማኩረፋቸውን ተገነዘቡ።

በመሆኑም ትራምፕ ለአለም ሰላም ሲባል የተፈጸመውን አለም አቀፍ ስምምነት ለአሜሪካ ጥቅም ሲሉ ውድቅ አደረጉት።

በኢራን ላይም የተጣለው ተጨማሪ ማዕቀብም ከጥቂት ወራት በኋላ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

አሜሪካ ይህ ማዕቀብ እንዲራዘም ብትፈልግም የመንግስታቱ ድርጅት የጽጥታው ምክር ቤት ማዕቀቡ እንደማይራዘም ከወዲሁ ወስኗል።

በዚህ ውሳኔ የተበሳጨችው አሜሪካ ወዳጆቿን ለማስደሰት ሌላ ማዕቀብ እንዲጣል እያሴረች መሆኑን የኢራን ፕሬዘዳንት ሀሰን ሮሀኒ ለአልጀዚራ ተናግረዋል።

ፕሬዘዳንቱ እንዳሉትም አሜሪካ እንደራደር ጥያቄ አቅርባልናለች ይሁንና ኢራን ወደ ድርድሩ የምትመለሰው አሜሪካ የ2015ቱን የኑክሌር ስምምነት ከተቀበለች ብቻ ነው ብለዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሳሙኤል አባተ
ነሀሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.