መንግስት የፖለቲካ አመለካከትን ለመደፍጠጥ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያቆም አብን አሳሰበ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ዛሬ ባወጣው መግለጫ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀመው «የዘር ማጥፋት ወንጀል» እንደሆነ ገልጿል።

ንቅናቄው በጥፋቱ የተሳተፉ፣ ሕዝቡን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግስት አመራሮችም በጉድለታቸው ልክ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን የመልሶ ማቋቋም ስራ እንዲሰራ ጥሪ ማቅረቡን አስታውሷል።

ጥቃቱ መፈፀም ከጀመረበት ዕለት አንስቶ የነቃ ክትትል በማድረግ በርካታ ወገናዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደቆየም ንቅናቄው ገልጿል፡፡

እንዲሁም ጥቃቱ ወደተፈፀመባቸው ቦታዎች በጊዜው በመንቀሳቀስ ዝርዝር ማስረጃዎችን ሰብስቦ እና አጠናቅሮ በልዩ ሁኔታ በጉዳዩ ዙሪያ ለሚሰሩ የአማራ ማኅበራት እና ተቋማት ማስተላለፉን በመግለጫው አሳውቋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርኔጋ ወረዳ ነሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈፀሙ ዘር-ተኮር ጥቃቶች ከአስራ አምስት(15) በላይ አማራዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን አረጋግጫለሁ በአካባቢም አሁም የጸጥታ ስጋት እንዳለም ለማወቅ ችያለሁ ነው የሚለው፡፡

የሕግ የበላይነትን በፅኑ እናስከብራለን በሚል በኦሮሚያ መንግስት እና የፌዴራል መንግስት የተገቡት ቃላት እንዲተገበሩም ጠይቋል፡፡

መንግስት ይሄን ታቅዶ እየተፈፀመ ያለ የዘር ማጥፋት እና ማፅዳት ወንጀል በአስቸኳይ እንዲያስቆም አብን ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ከነበረው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከታሰሩት ግለሰቦች መካከል የተወሰኑትን ጉዳይ ስንመለከት ወንጀልን በሰበብነት ተጠቅሞ የፖለቲካ አመለካከትን ለመደፍጠጥ ወይም ለጥፋተኞች የፖለቲካ ሚዛን መጠበቂያነት የማዋል ዝንባሌ እንዳለ ለመገንዘብ ችያለሁም ብሏል።

በመንግስት በኩል ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ ተጣርቶ ተገቢው እርምት እንዲሰጥ ንቅናቄው አሳስቧል።

ያለምንም ተጨባጭ ጥፋት በእስር ላይ የሚገኙት የአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱም አብን በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ነሀሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.