ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ከቤታቸው የተያዙት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ያለ ፍርድ እስር ቤት እንደሚገኙ ነው ጠበቃቸው የተናገሩት፡፡
የኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ጠበቃ የሆኑት አቶ አዲሱ ጌታነህ ደንበኛዬ ከተያዘ ሁለት ወር እንደሞላው ተናግረው በነዚህ ሁሉ ጊዜያቶች ውስጥ ፖሊስ ለምርመራ ጊዜ እየወሰደ ፍርድ ቤትም ተገቢ ያለውን ጊዜ እየሰጠ እስካሁን ድረስ ቆይተናል፡፡
ነገር ግን ፖሊስ ምርመራዬን ጨርሻለሁ ብሎ ለፍርድ ቤት ካስረከበ እና መዝገቡም ለአቃቢ ህግ የሰጠው ነሀሴ 13 ነው ስለዚህ የምርመራ መዝገቡ ከተዘጋ ኢንጂነር ይልቃል በዋስ መውጣት ይገባቸው ነበር ያ ግን ሊሆን አልቻለም ብለዋል፡፡
አቃቢ ህግ በእለቱ ቀርቦ ክስ ለመመስረት የ15 ቀን ቀነ ገደብ እንዲሰጠው ለፍርድ ቤት በደብዳቤ ጠይቆ ፍርድ ቤትም 10 ቀን በቂ ስለሆነ አቃቢ ህግ በዚህ ቀን ክስ እንዲመሰረት ሲል ትዛዝ ሰቶ ነበር፡፡
ነገር ግን ፍርድ ቤት የሰጠው ቀን ነሀሴ 22 ነበር ለሶስት ቀናት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይኖር ደንበኛዬ እስር ቤት ተቀምጠዋል ብለዋል ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ፡፡
የፍትህ ስርአት ማሻሻያ እየተደረገ ነው እየተባለ ባለበት ወቅት እንደዚህ ያሉ የመብት ጥሰቶች የሚደረጉ ከሆነ የህግ ስርአቱን ይጎጋዋል ሲሉም ተናግዋል አቶ አዲሱ፡፡
ደንበኛዬ አሁንም ቢሆን መጠርጠር የሚያስችል በቂ የሆነ ማስረጃ ያስፈልጋል ያሉት አቶ አዲሱ ከልክ በላይ ምርመራም ማድረግ አያስፈልግም ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሀሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም











