የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በቀጣይ ሁለት አመታት በሚያቀርባቸው የመድሃኒቶች ግዥ ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በአዲስ አበባ በመወያየት ላይ መሆኑን ለኢትይ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ብሔራዊ የመድኃኒት ግዥ መመሪያው በየሁለት አመቱ የሚከለስ ሲሆን የዛሬው ውይይትም በቀጣይ ስለሚደረጉ የህክምና ግብዓት ላይ ማተኮሩን ኤጀንሲው በመግለጫው አስታውቋል።
በዚህ ውይይት ላይ ከዚህ በፊት በነበረው ግዥ የሚስተካከሉ እንዲሁም እንደ አዲስ የሚካተቱ አዳዲስ የህክምና ግብአቶችን በቀጣይ በሚደረጉ ግዥዎች ላይ ለማካተት ታልሞ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በዚህ ውይይት ውስጥም በቀድሞ የመድሃኒት ዝርዝር ውስጥ የሌሉ ነገር ግን በተደጋጋሚ በጤና ተቋማት የሚጠየቁ፣የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አዳዲስ ፕሮግራሞች ማለትም ኩላሊት ንቅለ ተከላ አና ልብ ህክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች በአዲሱ ዝርዝር ውስጥ ትኩረት እንደተደረገባቸውም ተነግሯል፡፡
ኤጀንሲው ከአሁን በፊት 1 ሺህ 373 አይነት መድሀኒቶች፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች፣የመድሀኒት አቅርቦት፣ ኬሚካል አና ሬጀንቶች ውስጥ 489ኙን ቀንሷል።
እንዲሁም 140 የሚሆኑትን በመጨመር 1 ሺህ 24 አይነት ልዩ ልዩ የህክምና ግብአቶችን በቀጣይ ሁለት አመታት ለማቅረብ ባዘጋጀው እቅድ ላይ የሚመለከታቸው ተቋማት አመራሮች እና ባለሙያዎች በመወያየት ላይ ናቸው ተብሏል።
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በየውልሰው ገዝሙ
ነሀሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም











