ግብርና ሚኒስቴር በኮሮና ቫይረስ የሚጠቁ ሰራተኞች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ሰራተኞች እስከ መስከረም ድረስ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ አደረገ።

የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ በየጊዜው የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

በዚህ ቫይረስ ምክንያትም የጽኑ ህክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እና በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዕለታዊ መረጃ ያስረዳል።

ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት በርካታ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞቻቸውን ከቫይረሱ ለመጠበቅ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል።

ሰራተኞች በዓመት እረፍት እና በሌሎች መንገዶች መኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ እና በኢንተርኔት አማካኝነት ስራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ ከተወሰዱ የመከላከያ እርምጃዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ይሁንና ስራዎች የግድ መቀጠል ስላለባቸው በርካታ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞቻቸውን ወደ ቢሮ እነዲገቡ በማድረግ ወደ ስራ እንዲመለሱ አድርገዋል።

ከነዚህ መንግስታዊ ተቋማት መካከል የግብርና ሚኒስቴር አንዱ ሲሆን ወቅቱ የግብርና ስራዎች የሚከናወንበት ወቅት በመሆኑ እረፍት ላይ የነበሩ ሰራተኞቹን ወደ ቢሮ እንዲገቡ አድርጎ ነበር።

ይሁንና ሰራተኞች ወደ ቀድሞ ስራዎቻቸው ከተመለሱ በኋላ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰራተኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ኢትዮ ኤፍ ኤም ከተቋሙ ሰራተኞች ሰምቷል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የተቋሙ ሰራተኞች ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት እስካሁን ድረስ 70 ሰራተኞች በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

በቫይረሱ ከተጠቁ ሰራተኞች መካከልም የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን የጥበቃ እና ፕሮቶኮል ሰራተኞችን ይጨምራል።

አቶ ኡመር ሁሴን ጠባቂዎቻቸው በቫይረሱ መጠቃታቸው በምርመራ መረጋገጡን ተከትሎ ራሳቸውን አግልለው በቤታቸው ቆይተው አሁን ላይ በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ሰምተናል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰራተኞቹ ቁጥር መጨመሩ ያሳሰበው ሚኒስቴሩም ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ከወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ አስቸኳይ ስራዎችን ከሚያከናውኑ ውስን ሰራተኞች ውጪ ቀሪዎቹ በቤታቸው እንዲቆዩ እና ስራቸውን በኢንተርኔት እንዲያከናውኑ ማድረጉ ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበራ ለማ በበኩላቸው 90 በመቶ የሚኒስቴሩ ሰራተኞች ስራቸውን በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው እያከናወኑ መሆኑን ገልጸው በቫይረሱ የተጠቁ ሰራተኞች ቁጥር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በሳሙኤል አባተ
ነሀሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.