16 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ 19 ላብራቶሪ ማእከል ተመረቀ፡፡

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እጅግ ዘመናዊና የመርመር አቅሙ ከፍተኛ የሆነ የአዉቶማቲክ የኮቪድ 19 መመርመሪያ ላብራቶሪ ማዕከል መገንባት መቻሉን አስታውቋል፡፡

የወልቄጤ ዩኒቨርሲቲ የላብራቶሪ ማእከል በሀገራችን ደረጃ 54ኛው ማእከል እንደሆነ ዩንቨርሲቲው ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ሆሲፒታሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብድልሰመድ ወርቁ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቀጥሎ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ላብራቶሪ ነው ብለዋል፡፡

ላብራቶሪው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለመገንባት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀ የተናገሩት ዶ/ር አብድልሰመድ 6 ሚሊዮን ብሩ ከወልቂጤ የኒቨርሲቲ ቀሪዉ 10ሚሊዮን ብር የሚገመተው ቁሳቁስ ደግሞ ከተለያዩ 6 ተቋማት እንደተሸፈነ ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች የላብራቶሪ ማእከሉ በይፋ መርቀዉ ከፍተዋል፡፡

የኮቪድ 19 መመርመሪያ ማእከሉ ለጊዜው በቀን እስከ 5 መቶ ሰው እንደሚመረምር የተናገሩት ዶ/ር አብድልሰመድ ያልተሟሉ ቁሳቁሶች ሲሟሉ በቀን እስከ 1 ሺህ 5 መቶ ሰዎችን የመመርምር አቅም እንዳለዉ ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ይህን መልካም እድል በመጠቀም ተመርምሮ እራሱን እንዲያዉቅና ተገቢዉን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የምርመራ ማዕከሉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭቱ ሲያበቃ ለሌሎች በሽታ ለመመርመር እጅግ የሚጠቅም ተደርጎ የተገነባና ለጥናትና ምርምር ስራዎችም እንደሚጠቅም ተደርጎ የተሰራ ነው ተብላል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጷግሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.