ሐሰተኛ ማህተሞችን መቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ ማሽን ከውጭ አገር ገዝቶ ሊያስገባ መሆኑን የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በከተማዋ ከከተማ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ የወሳኝ ኩነት አደረጃጀት ውስጥ ተቀጥረው ከሚሰሩ ባለሙያዎች ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ መታወቂያን በማደል የተያዙ ባለሙያዎች መኖራቸውንም ኤጀንሲው አስታውቋል።

በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት በከተማዋ የሚገኙ አንዳንድ ህገ ወጥ አካላትና በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ በተሳሳተ መንገድ የነዋሪነት መታወቂያዎችን እና ሰነዶችን ሲሰጡ የተደረሰባቸው የኤጀንሲው ባለሙያዎች ላይ የቅጣት እርምጃ መወሰዱን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ ነጫ እንደነሩን በተጠናቀቀው በ2012 ከ 19 በላይ የሚሆኑ ሃሰተኛ ሰነዶችን በመስራት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘዋል።

እነዚህ ህገወጥ ስራን ሲሰሩ የተያዙ ባለሙያዎች ወደ ህግ መወሰዳቸውንና ወደ ፍርድ መቅረባቸውን ነግረውናል፡፡

ተቋሙ በተለያየ መንገድ ከ 2 ሺ በላይ ሃሰተኛ መታወቂያዎችን ፤ከ 70 በላይ የልደት ካርድ፤ 24 የጋብቻ ሰነዶችን በህገ ወጥ መንገድ እንደተዘጋጁ ሊደርስባቸው መቻሉን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት በተቋሙ ውስጥ ሲሰሩ በነበሩ ግለሰቦች ላይም እርምጃ መወሰዱን ነግረውናል፡፡

በዚህም በተቋሙ ፤በዲሲፕሊን ጥሰት የተቀጡ 6 ባለሙያዎች ፤በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታዩ ያሉ 5 ባሙያዎችና፤ 2 የተቋሙ ባለሙያዎች ከስራ ሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉንም ሰምተናል፡፡

ችግሩን ለመግታትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የነገሩን የተቋሙ ዶ/ር ታከለ ይህንን ዘማናዊ አሰራር ከመዘርጋት ጎን ለጎን ሃሰተኛ ማህተሞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ ማሽን በቅርቡ ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝም ነግረውናል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በየውልሰው ገዝሙ
ጷግሜ 3 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *