በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለስራ እድል ፈጠራ 400 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ አዲስ ስራ ጀማሪዎች ወደ ንግድ ሲገቡ ቢያንስ ለሶስት አመት ከግብር ነፃ እንዲሆኑ ወይንም እጅግ ዝቅተኛ ግብር አንዲከፍሉ የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በተጨማሪም ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ለስራቸው መንግስት ብድር እና የድጋፍ ብር እንዲያመቻችላቸው ያግዛል።
ረቂቅ አዋጁ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ጋር በመሆን አዲስ ስራ ፈጣሪዎች ሀሳባቸው ወደ ስራ እስከሚቀየር ድረስ በሂደቱ ከሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመጠበቅ በሚል መዘጋጀቱን ሰምተናል።
በስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሙሉጌታ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ረቂቁ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መሪነት ለፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የቀረበ ሲሆን አዋጁ ፀድቆ ሲወጣ አዲስ ስራ ፈጣሪዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ከመቅረፍ አንፃር አስተዎፆ ይኖረዋል ብለውናል።
በረቂቁ ከተካተቱት ዝርዝር ጉዳዮች መካከል አዲስ ስራ ፈጣሪዎች ወደ ቢዝነሰ ከገቡ በኃላ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ወይም አምስት ዓመታት ግብር እንዳይከፍሉ ያደርጋል ብለውናል።
አዲስ የስራ ፈጣሪዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲሰቃዩ ይስተዋላልና የውጪ ምንዛሬ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት የሚለውም በረቂቁ ተካቷል።
እንዲሁም የስራ ፈጣሪዎች እንደየ ቢዝነስ ሀሳቦቻቸው ከባንክ ከሚያገኙት ብድር በተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ የሚሆንላቸውን ፈንድ ማቋቋምንም ረቂቅ አዋጁ ይዟል ብለውናል አቶ ዳዊት።
አቶ ዳዊት እንዳሉት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለስራ እድል ፈጠራ 400 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋታል።
የስራ እድል ፈጠራን በሚመለከት ወጣቶች ስራ ፈጣሪ እና በተሰማሩበት መስክም ውጤታማ እንዲሆኑ በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰራውና መቀመጫውን ኔዘርላንድ ያደረገው ኮርዴኤይድ የተባለው ድርጅትም ከዚሁ ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ፤ የወጣቶችን አቅም ከማዳደግ አንፃር በሚረዱ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ከስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከንግድና ኢንድስትሪ ሚንስቴር እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑንም ሰምተናል።
በትግስት ዘላለም
ጷግሜ 3 ቀን 2012 ዓ.ም











