የሁለት ልጆቹን እናት የገደለው ተከሳሽ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

የጸቡ መንስኤ ባልታወቀ ሁኔታ ጨካኝነቱን በሚያሳይ ሁኔታ የሁለት ልጆቹን እናት የገደለው ተከሳሽ በተመሰረተበት ክስ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታውቋል፡፡

የክሱ ዝርዝር እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ሀብቴ ግርማ የጦር መሳሪያ አስቀድሞ በማዘጋጀት እና ወንጀል ለመፈጸም አመቺ ግዜ በመጠበቅ ህጋዊ ሚስቱን እና የሁለት ልጂቹን እናት የጸቡ መንስኤ ባልተወቀ መነሻ ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 6፡00 ሰዓት በአራዳ ክ/ከተማ በሚገኘው በመኖሪያ ቤት ውስጥ ጨካኝነቱን፣ ነውረኛነቱን እና አደገኛነቱን በሚያሳይ ሁኔታ በልጆቹ ፊት ሟችን በማንበርከክ በያዘው ሽጉጥ ተኩሶ በመምታት ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በክሱ መሰረት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማደራጀት ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለቱ ምስክሮች ቀርበው ተሰምተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሽን በፈጸመው ድርጊት ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ ነሀሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ተከሳሽን በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ጷግሜ 3 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *