ኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ የሞባይል አገልግሎት ደንበኞቹ በተለያዩ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋበት ጊዜ ወዲያውኑ እያዘጉ አይደለም ብሏል።
በተጨማሪም ደንበኞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸው የተነሳ ወንጀለኞች የስልክ መስመሩን ለተለያዩ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች እየተጠቀሙበት ነውም ብሏል።
በዚህ ምክንያትም ኩባንያውን ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እየዳረጉ እንደሆነ አስታውቋል።
ኩባንያው በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት በመዘርጋት ቀደም ሲል የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን በመጠቀም ሲፈጽሙ የነበሩ የማጭበርበር ወንጀሎችንን የቀነሰ ቢሆንም ህገወጦች በደንበኞች በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት በመጠቀም የሚፈጽሙት የማጭበርበር ድርጊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝም ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2012 ዓ.ም ብቻ በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የተፈጸመ ሲሆን በዚህም ኩባንያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ኪሳሬ እንደገጠመው አስታውቋል።
በመሆኑም ኩባንያው ደንበኞቹ በተለያየ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋባቸው ጊዜ ወደ ኩባንያው 994 የጥሪ ማዕከል በመደወል በ8994 አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ወይም ይፋዊ የማህበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም ወዲያውኑ መስመራቸውን እንዲያዘጉ አሳስቧል።
እንዲሁም በአቅራቢያቸው በሚገኝ የሽያጭ ማዕከል ምትክ ሲም ካርድ እንዲወስዱ እና የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው እንዳይሰጡ አሳስቧል።
በሳሙኤል አባተ
መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም











