በአለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ 19 የሞተው ሰው ቁጥር ከ 1 ሚሊዮን መሻገሩ ድንጋጤን ፈጥሯል።

በአለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ 19 ህይወታቸው ያለፈ ቁጥር አንድ ሚሊዮን ያለፈ ቢሆንም አሁንም የተጠቂዎችና የሟቾች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን አጥኚዎች እየተናገሩ ነው፡፡

በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሜሪካ፣ በብራዚል እና በህንድ ያለው የሟች ቁጥር በአለም ላይ ከሞተው ቁጥር ግማሹን ይይዛል፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት ትክክለኛ የሟቾችና የተጠቂዎች ቁጥር ቢታወቅ ከዚህም በጣም ከፍ ሊል ይችላል ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እየተሰማ ያለው የተጠቂና የሟች ቁጥር አይምሮ ያደነዝዛል ያሉ ሲሆን አሸማቃቂና አሳዛኝ ሲሉ ገልፀውታል፡፡

አሁን የእያንዳንዱን ግለሰብ ህይወት ለመታደግ መደረግ ያለበት ሁሉ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

አባቶችና እናቶች፣ ሚስቶችና ባሎች ወንድሞችና እህቶች ፣ ጓደኞችና የስራ ባልደረቦች ናቸው ህይወታቸው በበሽታው የተቀጠፈው ሲሉ ተናግረዋል ጉቴሬዝ፡፡

ወራርሽኙ ከ 10 ወር በፊት በቻይናዋ ውሀን ከተማ ከተሰማ ጀምሮ የቫይረሱ ስርጭት ከነጭካኔውና ከነአስቀያሚነቱ እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡

በ188 ሀገራት 32 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡

ቫይረሱን ለማቆም በተደረጉ ጥረቶች የብዙ ሀገራት ኢኮኖሚ ደቋል፡፡

ውጤታማ ክትባት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የቀጠለ ሲሆን ክትባቱ እሲኪገኝ የሟቾች ቁጥር 2 ሚሊዮን ሊሻገር ይችላል ሲል የአለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡

አሜሪካ ከፍተኛውን የሟች ቁጥር ያስመዘገበች ሲሆን 205 ሺህ ዜጎቿ ሞተውባታል፣ ብራዚል 141 ሺህ 700 ዜጎቿ በቫይረሱ ሞተውባት በሁለተኝነት ስትቀመጥ 95 ሺህ 500 ዜጎቿን ያጣችው ህንድ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሰው በቫይረሱ ያጣች ሶስተኛዋ ሀገር ነች፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.