ባደጉት ሃገራት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን ይህንን አሰራር በመዲናዋ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች እየተገባደዱ መሆኑን ኢትዮ ኤፍኤም ሰምቷል፡፡
ጎ አይ ዲ የተሰኘው የኦን ላይን ቴክኖሎጂ የመዲናዋ ነዋሪዎች መታወቂያውን ለማውጣት የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ሲያሟሉ ባሉበት ቦታ ላይ ሆነው በቀላሉ ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የነዋሪነት መታወቂያቸውን የሚያገኙበት ስርዓት መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የዋና ዳሬክተር አማካሪ የሆኑት አቶ መላክ መኮንን ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ይህንን አሰራር በዚሁ በያዝነው ዓመት ወደ ተግባር ለማምጣት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውንም ሰምተናል፡፡
ቴክኖሎጂውን በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በሙከራ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ስልጠናዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
ለዚህም የሚያግዙ ከ 32 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች በሁሉም ወረዳዎች መሰራጨታቸውን አቶ መላክ ነግረውናል፡፡
ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር ለማውረድ በቅድሚያ ጥናት መደረጉን ያነሱት አቶ መላክ ምን ያክሉ የከተማዋ ነዋሪ የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚ ነው? የሚሉ ጉዳዮች በጥናቱ መካተታቸውንና፤ ቴክኖሎጂው የፎርጅድ ዶክመንቶችን ለማስቀረት ያለው ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑ አሰራሩን ማስጀመር ማስፈለጉ ነግረውናል፡፡
በቅርቡም ጎ አይ ዲ የተሰኘውን የመዲናዋ ነዋሪዎች በአንድሮይድ ስልካቸው ባሉበት ቦታ ሆነው የነዋሪነት መታወቂያ መስፈርትን ሲያሟሉ መታወቂያውን ለማግኘት የሚያስችላቸውን የኦን ላይን ቴክኖሎጂ ወደ ስራ እንደሚገባ ኤጀንሲው ለኢትዮ ኤፍኤም አስታውቋል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በየውልሰው ገዝሙ
መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም











