የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ተማሪዎች ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጥሪ ይደረግላቸዋል በሚል የተሰራጨው ዜና ስህተት መሆኑ ተገለፀ፡፡

ከሰሞኑ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮችን የተሳተፉባቸው ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡

በዋናነት በጅማ ዩንቨርሲቲ ሲካሄድ የቆየው የሦስት ቀናት ጉባኤ እንዲሁም በጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት የተካሔዱ ውይይቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የ2013 ዓ.ም ትምህርት በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ የመከረው ጉባኤ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ተማሪዎች ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጥሪ እንደሚደረግላቸው በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መገለፁን ከተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሰምተናል።

ይሁን እንጂ ኢትዮ ኤፍ ኤም ያነጋገራቸው የባህርዳር ፤ የድሬደዋ እና የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች ባለፈው ሳምንት የ45 ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በጅማ ሲያካሂዱት በቆየው የሦስት ቀናት ጉባኤ ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎቻችሁን ተቀበሉ የሚል አቅጣጫ አለመቀመጡን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤምም የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ተማሪዎች ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጥሪ ይደረግላቸዋል የሚለው ዜና ከመሰራጨቱ በፊት በጊዜ ገደቡ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እንዲጠሩ የተቀመጠ አቅጣጫ ሳይኖር መረጃውን ለምን ማሰራጨት አስፈለገ ስንል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን ጠይቋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጉርሙ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለፁት በወቅቱ በነበረው ውይይት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ተማሪዎች ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጥሪ እንደሚደረግላቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል በሚል የተሰራጨው ዘገባ ስህተት ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በምክረ ሀሳብ ደረጃ የተነሳ እንጂ ውሳኔ ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው በሰዓቱ የተገኙ ሚዲያዎች የተሳታፊዎችን ሀሳብ በመውሰድ በስህተት የዘገቡት መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

ትምህርት ማስጀመርን በተመለከተ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መመሪያ የተሰጠ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደቻሳ ከዛሬ ጀምሮ ይህንን የሚገመግም ቡድን እናሰማራለን ብለዋል፡፡

ቡድኑ አጠቃላይ የግምገማ ሪፖርቱን እንዳደረሰን እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎቹን የሚጠራበትን ጊዜ ወደ ፊት እናሳውቃለን በማለት ነግረውናል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በደረሰ አማረ
መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *